የመልካም አስተዳደር መስፈን ለመማር ማስተማር ሥራ ወሳኝ ነው

የህክምናና ጤና ሣይንስ ኮሌጅ በመልካም አሰተዳደር ዙሪያ ከተማሪዎች፣ ከመምህራን እና ከአስተዳደር ሰራተኞች ጋር ታህሳስ 7/2009 ዓ.ም ውይይት አካሂዷል፡፡

የውይይቱ ዓላማ በ2009 የትምህርት ዘመን በመማር ማስተማርና በአገልግሎት አሰጠጥ ላይ የታዩ ክፍተቶችና ጠንካራ አፈጻጸሞች በመለየት፣ ደካማ አፈፃፀሞችን በማሻሻልና መልካም አፈፃፀሞች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በማድረግ ለኮሌጁ ማህበረሰብ የተሻለ አገልግሎት መስጠት ነው ሲሉ የህክምናና ጤና ሣይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ታምሩ ሽብሩ ገልፀዋል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የህክምናና ጤና ሣይንስ ኮሌጅ የሠላም ፎረም ተጠሪ ተማሪ ወገኔ አሰፋ በአስተያየቱ መምህራን፣ ተማሪዎችና የአስተዳደር ሠራተኞች በግልጸኝነት በክፍተቶች ላይ ተነጋግረው የአጭርና የረጅም ጊዜ ዕቅድ በመንደፍ ሠላማዊ የመማር ማስተማር እንዲሰፍንና ተማሪዎች ያለምንም እክል ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ውይይቱ ጉልህ ሚና አለው ብሏል፡፡

የመማሪያና ቤተ-ሙከራ ክፍሎች፣ የቤተ-ሙከራ መሳሪያዎች፣ ጥበቃና ደህንነት፣ በሆስፒታል የሚሰጡ የተግባር ሥልጠናዎች፣ የሠራተኞች ሰርቪስ አሰጣጥ፣ የኮርስ አሰጣጥና አጨራረስ፣ የመፀዳጃ ቤት አገልግሎትና የአለባበስ ሥነ-ሥርዓት በውይይቱ ከተነሱ ነጥቦች መካከል ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ በውይይቱ የተነሱ ነጥቦችን ለየሚመለከተው የሥራ ክፍልና ዲፓርትመንት በማከፋፈል ችግሮች በየደረጃው እንዲፈቱ በማድረግ አገልግሎት አሰጣጡን ለማሳደግ ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበት ተሳታፊዎች አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

በውይይቱ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ መምህራን፣ ተማሪዎችና የአስተዳደር ሠራተኞች ተሳትፈዋል፡፡