የህፃናት ጉልበት ብዝበዛን አስመልክቶ ዓውደ ጥናት ተካሄደ

የሶሲዮሎጂና ሶሻል አንትሮፖሎጂ ትምህርት ክፍል ከኢትዮጵያ ሶሲዮሎጂስቶች፣ ሶሻል ወርከርስ እና አንትሮፖሎጂስቶች ማኅበር ጋር በመተባበር በጋሞ ከፍተኛ ቦታዎች በሚገኙ ህፃናት ላይ የሚደርሰውን የጉልበት ብዝበዛ አስመልክቶ ኅዳር 30/2009 ዓ/ም ዓውደ ጥናት አካሂዷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

 

የዓውደ ጥናቱ ዓላማ በህፃናት ላይ የሚደርሰውን የጉልበት ብዝበዛ ለማስቀረት የፍትህና የባለ ድርሻ አካላት ሚናን በመገምገምና በቂ ግንዛቤ በማስጨበጥ ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት መሆኑን የትምህርት ክፍሉ ኃላፊ መ/ር ተመቸኝ እጉቱ ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሶሲዮሎጂስቶች፣ ሶሻል ወርከርስ እና አንትሮፖሎጂስቶች ማኅበር ባላሙያ አቶ ዘላለም አንተነህ እና በጫሞ ካምፓስ የሥነ-ዜጋና ሥነ-ምግባር መምህር አቶ አስታጥቄ ዓለሙ  በጥናታዊ ጽሑፎቻቸው እንዳብራሩት አካላዊ፣ ስነ-ልቦናዊና ፆታዊ ጥቃቶች እንዲሁም ማግለልና ወልዶ መጣል በህፃናት ላይ ከሚደርሱ ጥቃቶች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ በበኩላቸው ድህነት፣ መገለል፣ የሥራ መደራረብና መሠል ነገሮች ለህፃናት ጉልበት ብዝበዛ ምክንያቶች ሲሆኑ ዩኒቨርሲቲው የማህበረሠብ አገልግሎቱን በማጠናከር ለችግሮቹ ዘላቂ እልባት ለማግኘት ይሠራል ብለዋል፡፡

የህፃናት ጉልበት ብዝበዛን ለመከላከል ዩኒቨርሲቲው ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ለማህበረሠቡ የቤተሠብ ምጣኔ ትምህርትና የምክር  አገልግሎት  በመስጠትና ለውጦችን በመገምገም ተጠናክሮ መሥራት እንደሚጠበቅበት ተሳታፊዎች አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

በአውደ ጥናቱ የዞን ሴቶችና ህፃናት መምሪያና የዞን ፖሊስ መምሪያ ተሳታፊዎች እንዲሁም የሶሲዮሎጂና ሶሻል አንትሮፖሎጂ ትምህርት ክፍል ተጠሪዎችና ተማሪዎች  ተገኝተዋል፡፡