በዓለም ለ13ኛ ጊዜ በሀገራችን ለ12ኛ ጊዜ የሚከበረው የፀረ-ሙስና ቀን በዩኒቨርሲቲው ለ3ኛ ጊዜ ‹‹ሙስናንና ብልሹ አሠራርን መከላከል ለህዳሴያችን›› በሚል መሪ ቃል ጥር 18/2009 ዓ/ም በዋናው ግቢ በደማቅ ሥነ-ሥርዓት ተከብሯል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

በዕለቱ ሙስናና ብልሹ አሠራርን የመከላከል አስፈላጊነትና ስትራቴጂ ላይ የመወያያ ሰነድ የቀረበ ሲሆን በተጨማሪም ከበጀት አጠቃቀም፣ የሙስና ጽንሰ ሀሳቦች ላይ ግንዛቤ በመፍጠር ተተኪውን ትውልድ በሥነ ምግባር ከማነጽ፣ ግልጽ የአሠራር ሥርዓት ከመዘርጋት እና ህጋዊ እርምጃዎችን ከመውሰድ አንፃር ዩኒቨርሲቲው በሚያከናውናቸው ተግባራት ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡

በመወያያ ሰነዱ እንደተገለፀው ሀገራችንን ለረዥም ዘመናት ተብትቦ ከያዛት ድህነት ለማውጣት አበረታች የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ሲሆን የህዝቡን የልማት ጥያቄ ትርጉም ባለው ሁኔታ ለመፍታትና ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ መሰናክል ከሆኑ ችግሮች አንዱና ዋነኛው ሙስናና ብልሹ አሠራር ነው፡፡

የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ራሱን ከብልሹ አሠራር ጠብቆ የሀገሪቱን ህዳሴ እንዲያፋጥን በተለያዩ ጊዜያት የማነቃቂያ ሥልጠናዎች እየተሰጡ መሆኑን  የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ዳይሬክቶሬት ተ/ዳይሬክተር አቶ ዮሴፍ ወርቁ ገልፀዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በበኩላቸው ሙስናና ብልሹ አሠራር በማደግ ላይ ላሉም ሆነ ላደጉ ሀገራት የልማት ማነቆ መሆኑን ጠቅሰው የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሙስናን በመዋጋት ሀገራችን በምታካሂደው ልማት ዋነኛ ተዋናይ እንዲሆን አሳስበዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ የሥራ ክፍል ኃላፊዎች፣ የቡድን መሪዎች፣ ተማሪዎችና ሌሎች የግቢው ማህበረሰብ አባላት በዓሉን ታድመዋል፡፡