በተፈጥሮ ሣይንስ ኮሌጅ የሒሳብ ትምህርት ክፍል በጥናትና ምርምር አዘገጃጀትና ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ዙሪያ ለትምህርት ክፍሉ መምህራን ከጥር 4–10/2009 ዓ.ም የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡

የትምህርት ክፍሉ ኃላፊ መ/ር ተሾመ ባይለየኝ እንደተናገሩት የሥልጠናው ዓላማ በመማር ማስተማር የመምህራንን አቅም ማጎልበት፣ በሒሳብ ትምህርት መሠረታዊ ፅንሰ-ሃሳብ ላይ ግንዛቤ ማስጨበጥ፣ መምህራን የሚገጥሟቸውን አካዳሚያዊ ችግሮች በቀላሉ መፍታት የሚችሉበትን ዘዴ መወያየት እና የምርምር ሥራዎቻቸው ችግር ፈቺ እንዲሆኑ ማስቻል ነው፡፡

ሥልጠናው ከአሜሪካ ቴምፕል ዩኒቨርሲቲ በመጡ የዘርፉ ምሁር ፕሮፌሰር ሽፈራው ብርሃኑ የተሰጠ ሲሆን በዋናነት በመሠረታዊ የሒሳብ ትምህርት ፅንሰ-ሃሳብ፣ በጥናትና ምርምር አዘገጃጀት እና በዘርፉ ለሚያጋጥሙ ችግሮች በቀላሉ መፍትሔ ማፈላለግ ላይ ያተኮረ ነው፡፡

ሠልጣኞች በሰጡት አስተያየት ሥልጠናው ግንዛቤ የሚያስጨብጥ እና የሚያጋጥሙ ችግሮችን በቀላሉ መፍታት የሚችሉበትን ዕውቀት እንዳገኙ ገልፀው መሰል ሥልጠናዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል፡፡

በሥልጠናው 29 የትምህርት ክፍሉ መምህራንና የፒኤችዲ ተማሪዎች ተሳትፈዋል፡፡