ዩኒቨርሲቲው የአርባ ምንጭ እና የሳውላ 2ኛ ደረጃና መሰናዶ ት/ቤቶችን ወደ ልህቀት ማዕከልነት ለማሸጋገር የሦስት ዓመት ተኩል ስትራቴጂክ ዕቅድ ሰነድ አዘጋጅቶ የካቲት 2/2009 ዓ.ም ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡ ትምህርት ቤቶቹን ወደ ልህቀት ማዕከልነት ለማሳደግ ቀደም ሲል የዳሰሳ ጥናት ተከናውኖ ምክክር ተደርጎበታል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

 

የውይይቱ ዓላማ ትምህርት ቤቶቹ ያሉባቸውን ተግዳሮቶች በመለየትና በመደገፍ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ማብቂያ የልህቀት ማዕከል እንዲሆኑ ማስቻል ነው ሲሉ የማ/አገ/ዳይሬክቶሬት ተወካይ ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ ተናግረዋል፡፡ ቀደም ሲል ት/ቤቶቹ ያሉበትን ነባራዊ ሁኔታ የሚያሳይ የዳሰሳ ጥናት ቀርቦ የጋራ ግንዛቤ የተፈጠረ ሲሆን ጥናቱን መነሻ በማድረግ የሥነ-ትምህርት ባለሙያዎችንና የትምህርት ባለድርሻ አካላትን ባካተተ ዓብይ ኮሚቴ የተዘጋጀው ስትራቴጅክ ዕቅድ የባለድርሻ አካላትን ቀጣይ ሚና የሚያመላክትና የሥራ ድርሻቸውን የሚያሳውቅ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በበኩላቸው የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ ትምህርት ቤቶች የሣይንስና ቴክኖሎጂ ተመራማሪዎችን እንዲሁም የፈጠራ ሥራ ባለቤት ተማሪዎችን የሚያፈሩና ለዩኒቨርሲቲ የሚያበቁ እንዲሆኑ ግብዓቶችን ማሟላት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የፕሮጀክት ቀረፃ፣ ትግበራ፣ ግምገማና ቁጥጥር ከፍተኛ ኤክስፐርት አቶ ሸዋረታ ጌታቸው ስትራቴጂክ ዕቅዱን ሲያቀርቡ እንደገለፁት የትምህርት ጥራትን ማስጠበቅ በሀገር አቀፍ ደረጃ ትኩረት የተሰጠው በመሆኑ የበቁና የላቁ ተማሪዎችን ለማፍራት የልህቀት ማዕከላትን ማደራጀት አስፈላጊነቱ ጉልህ ነው፡፡ ዕቅዱን ለማስፈፀም ይረዳ ዘንድም ባለድርሻ አካላትን ማሳተፍ፣ ቅንጅታዊ አሠራሮችን መፍጠር፣ የታዩ ክፍተቶችን መሙላትና መደገፍ እንዲሁም የክትትልና ቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋት ቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡

ሊካተቱ የሚገባቸው ጉዳዮች፣  የፈፃሚና የአስፈፃሚ አካላት ድርሻ፣ የግብዓቶች ጥራት ደረጃ ተቆጣጣሪ ቡድን፣ ወደ ማዕከሉ ለሚገቡ ተማሪዎች የመግቢያ መመዘኛ መስፈርት እና ከተማሪ ወላጆች ጋር ተቀናጅቶ መሥራት በውይይቱ የቀረበውን ሰነድ ተከትሎ ከተሳታፊዎች የተነሱ  ሃሳቦች ናቸው፡፡

ስትራቴጅክ ዕቅዱን መሠረት አድርጎ ወደ ቀጣይ ትግበራ ሂደት ለመግባትና ለአፈፃፀሙ ስኬታማነት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቁርጠኝነት ተቀናጅተው መሥራት እንደሚጠበቅባቸው እንዲሁም የዞኑ ትምህርት መምሪያ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ አፈፃፀሙን ከዩኒቨርሲቲው ጋር እንዲገመግም የጋራ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

በውይይቱ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች፣ የማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊዎች፣ የዞን ትምህርት መምሪያና የከንቲባ ጽ/ቤት ኃላፊዎች እንዲሁም የትምህርት ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡