የግብርና ሣይንስ ኮሌጅ Sasakawa Africa Fund for Extension Education ከተሰኘ ድርጅት ጋር በመተባበር ‹‹Agricultural Value Chain at Small Holder Farmer›› በሚል ርዕስ የካቲት 7/2009 ዓ/ም ዓውደ ጥናት አዘጋጅቷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

 

የዓውደ ጥናቱ ዓላማ ድህረ ምርት እሴቶችን በመጨመርና የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ምርቶች ገበያ ተኮር እንዲሆኑ ለማስቻል መምህራን በግብርና ምርት እሴት ጭመራ ላይ ያላቸውን ግንዛቤና ልምድ በማዳበር ለተማሪዎቻቸው ዕውቀትን የሚያካፍሉበትንና ለአርሶ አደሩ ተደራሽ የሚሆንበትን መንገድ ማመቻቸት መሆኑን የገጠር ልማትና ግብርና ኤክስቴንሽን ትምህርት ክፍል ኃላፊ መ/ር አማኑኤል ሸዋ ገልፀዋል፡፡

የደቡብና ምሥራቅ አፍሪካ Sassakawa Africa Fund for Extension Education Program አስተባባሪ ዶ/ር ጀፍ ሙቲምባ አርሶ አደሩ በሚያመርተው ምርት ላይ እሴትን በመጨመር ገቢን ከማሳደግ አንፃር ምን ማድረግ እንደሚገባው የሚያሳይ ፅሁፍ አቅርበዋል፡፡ መምህራን ያገኙትን ክህሎት ለተማሪዎች በማካፈል የግብርና ሂደት እንዲያድግድና አመርቂ ውጤት እንዲያመጣ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ሊያበረክቱ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

አስተባባሪው እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ዲፕሎማ ያላቸውን ተማሪዎች በግብርና ኤክስቴንሽን በክረምት የዲግሪ ፕሮግራም በማስተማር በዘርፉ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው፡፡ ተማሪዎቹ ለዘመናዊ ግብርና ቁልፍ ሚና ያላቸው በመሆኑ ከሣይንሱ ባሻገር ለድህረ-ምርት ውጤታማነት የሚያስፈልገውን ክህሎት በመለየት ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እንዲያደርጉ የሚያስችላቸውን መንገድ ማሳየት ተገቢ ነው፡፡

በSasakawa Global 2000 ፕሮጀክት የድህረ -ምርት አግሮ ፕሮሰሲንግ አስተባባሪ ወ/ሮ አበራሽ ፀሐይ በድህረ-ምርት ላይ ያላቸውን ልምድ ሲያካፍሉ እንደተናገሩት ከዚህ ቀደም በምርት ሂደት ላይ ብዙ የተሠራ ቢሆንም በድህረ-ምርት ላይ ትኩረት ሳይሰጥ ቆይቷል፡፡ Sasakawa Global 2000 ፕሮጀክት ጊዜና ጉልበት ቆጣቢ እንዲሁም ጥራትን የሚያሻሽሉ ዘመናዊ የማጨጃ፣ የመውቂያ፣ የመፈልፈያ እና  ምንም ዓይነት ኬሚካል ሳይጨመር አየርን በማፈን ብቻ ምርትን ከዓመት እስከ አመት ሳይበላሽ የሚያቆይ የተሻሻለ የእህል ጎተራ ቴክኖሎጂን በማስተዋወቅ ላይ እንዳለም ተናግረዋል፡፡ አርሶ አደሩ የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በተለይ በድህረ-ምርት የሚደርስበትን የእህል ብክነትና የጥራት ጉድለት እንዲያስቀርና ጊዜውን እንዲቆጥብ ለማስቻል ኮሌጁ ወደ አርሶ አደሩ ወርደው የሚሠሩ ባለሙያዎችን የሚያፈራ በመሆኑ መምህራን የተለያዩ ልምዶችን በመቅሰም ለሚያስተምሯቸው ተማሪዎች ዕውቀትን ማስጨበጥ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

የምርት ሂደት ከጅምር እስከ ፍፃሜ ጥራቱን ጠብቆ እንዴት ለገበያ መቅረብ እንዳለበት የገለፁት የSasakawa Global 2000 ፕሮጀክት ባለሙያ አቶ በሬቻ ቱሪ ገበያና አርሶ አደሩን እንዴት ማገናኘት እንደሚቻልና አነስተኛ ገበሬዎች ምርታቸውን ለገበያ ማቅረብ የሚችሉበትን ሁኔታ በአውደ ጥናቱ ገልፀዋል፡፡

በዓውደ ጥናቱ ድህረ-ምርት ላይ ያተኮሩ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ተነስተው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ከዓውደ ጥናቱ ለመማር ማስተማር ሥራ ስኬት ብሎም በግብርናው ዘርፍ በርካታ አስተዋፅኦ የሚያበረክቱ የተለያዩ ልምዶችን መቅሰማቸውን ተናግረዋል፡፡