በጤና ሣይንስ ኮሌጅ ሥር የተቋቋመው ትኩረት የሚሹ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች ምርምርና ሥልጠና ማዕከል መጠነ ሰፊ የመድኃኒት ሥርጭት የተናጥል ቁጥጥር ሁለተኛ ዙር አፈፃፀምና የምርምር ንድፈ-ሀሳቦች ማስተቸትን አስመልክቶ የካቲት 4/2009 ዓ/ም ዓውደ ጥናት አካሂዷል፡፡

የአስ/ጉ/ም/ፕሬዝደንትና የማዕከሉ መሥራች አቶ በኃይሉ መርደኪዮስ እንደተናገሩት ማዕከሉ በሚያከናውናቸው ጅምር የጣምራ ተግባራት ዩኒቨርሲቲው የገነባውን መልካም ስም በማጠናከር ማህበረሰቡን በስፋት ተጠቃሚ ለማድረግና በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን በዘርፉ የልህቀት ማዕከል የመሆን ራዕዩን ለማሳካት እየሠራ ነው፡፡

ማዕከሉ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በተሰጠው ተልዕኮ በጋሞ ጎፋ ዞንና በሌሎችም የሀገራችን አካባቢዎች በርካቶችን ለአካል መጉደልና ለህልፈት የሚዳርጉ የካላዛር፣ ትራኮማ፣ ቢልሃርዚያ፣ የሆድ ጥገኛ ትላትል እና ዝሆኔ በሽታዎችን መከላከል የሚያስችል ሥራ በትብብር እየሠራ እንደሚገኝ የማዕከሉ ዳይሬክተር ወ/ሮ ትዕግሥት ገዝሙ ገልፀዋል፡፡ የኢፌዴሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴርም በሽታዎቹን ለመግታት እንዲያስችል ከተለያዩ መንግስታዊ ያልሆኑ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች በሚያገኘው ድጋፍ በመታገዝ ዕድሜያቸው ከ19 ዓመት በታች ለሆኑ ልጆች በዓመት ሁለት ጊዜ የሆድ ጥገኛ ትላትል እና የቢልሃርዚያ መድኃኒትን በማዳረስ ላይ ይገኛል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በማዕከሉ በኩል ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ፣ ከክልሎች፣ ከዞኖችና ከወረዳዎች ጋር በመቀናጀት የመድኃኒት ሥርጭትና አሰጣጥ ሁኔታ ላይ ሙያዊ ግምገማ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

በኮሌጁ የምርምርና ማህበረሰብ አገ/ት አስተባባሪ በአቶ አለሙ ጣሚሶ አማካኝነት ትኩረት የሚሹ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች ምርምርና ሥልጠና ማዕከል የተናጥል የመድኃኒት ሥርጭት ቁጥጥር ሥራን (Independent Monitoring) አስመልክቶ አጠቃላይ ገለጻ የተደረገ ሲሆን በጤና ሣይንስ ኮሌጅ መምህራን በዘርፉ የተሠሩ 10 የጥናትና ምርምር ንድፈ-ሀሳቦች በዓውደ ጥናቱ ቀርበው በተሳታፊዎች ተተችተዋል፡፡

የማዕከሉን አደረጃጀት ለማሻሻል በሰው ኃይልና በፋይናንስ መደገፍ፣ ከተለያዩ ረጂ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት መፍጠር፣ የምርምርና ሥልጠና ማዕከሉን የተግባር ወሰን ማስፋት፣ ማዕከሉ በዋናነት የተቋቋመበትን ዓላማ ከማሳካት አንጻር ከመድኃኒት ሥርጭት በተጓዳኝ እየተከናወኑ ስላሉ ተግባራት እና ሌሎች ተግዳሮቶችን በሚመለከት ከተሳታፊዎች አስተያየቶችና ጥያቄዎች ቀርበዋል፡፡ ለዚህም የቀድሞው የኮሌጁ ዲንና ማዕከሉ እንዲቋቋም ትልቅ ሚና የነበራቸውና በአሁኑ ወቅት በዩኒቨርሲቲው የአስተዳደር ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት አቶ በኃይሉ መርደኪዮስና በማዕከሉ ዳይሬክተር ወ/ሮ ትዕግሥት ገዝሙ አማካኝነት ሰፊ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡ ከተናጥል የመድኃኒት ሥርጭት ቁጥጥር (Independent Monitoring) ባሻገር ማዕከሉ በዋናነት በታቀዱ ተግባራትና አደረጃጀቱን የማጠናከር ሂደት ላይ በትኩረት እንደሚሠራም ተገልጿል፡፡

ማዕከሉ ባስመዘገበው የተሻለ የ2 ዙር አፈፃፀም መሠረት ለ3ኛ ዙር መመረጡ የተገለፀ ሲሆን ለ3ቱም ዙሮች በጥቅሉ 5.6 ሚሊዮን ብር በጀት ተመድቦ እየተሠራበት ይገኛል፡፡

በፕሮግራሙ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ የህክምናና ጤና ሣይንስ ኮሌጅ መምህራንና ሌሎች ከ50 በላይ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡