የዩኒቨርሲቲው ስፖርት አካዳሚ ከጋሞጎፋ ዞን ወረዳዎች እና ከተማ አስተዳደሮች ለተወጣጡ 26 የስፖርት መምህራን እና ባለሙያዎች የአትሌቲክስ ስፖርት የመጀመሪያ ደረጃ የአሠልጣኝነት ሥልጠና በደቡብ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮና በአዳማ ሣይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ከየካቲት 1-10 /2009 ዓ.ም ሰጥቷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

 

ሥልጠናው በንድፈ-ሃሳብና በተግባር የተሰጠ ሲሆን ከተግባር ሥልጠናዎች ከ100 ሜትር ጀምሮ የአጭር ርቀት ሩጫ ፣ የዲስከስ፣ አሎሎና ጦር ውርወራ እንዲሁም የከፍታ ዝላይ ተካተዋል፡፡

የሥልጠናው ዓላማ የአትሌቲክስ ስፖርት መርሆዎችን መሠረት በማድረግ ደንብና መመሪያን ተከትሎ ውጤታማ የሚሆን አሰልጣኝ ማፍራት እንደሆነ በአዳማ ሣይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የአትሌቲክስ መ/ርና ዓለም አቀፍ የሁለተኛ ደረጃ የአትሌቲክስ ስፖርት አሰልጣኝ ኢንስትራክተር ጌታቸው ዘውዴ ተናግረዋል፡፡

የደቡብ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የአትሌቲክስ ስፖርት ኢንስትራክተር አቶ ሰይፉ ዓለሙ እንደገለፁት የአትሌቲክስ ስፖርትን ለማስረጽና ደረጃውን ለማሳደግ በተለይ ትምህርት ቤቶች ሰፊውን ድርሻ ይይዛሉ፡፡ በመሆኑም በአትሌቲክስ ስፖርት ተተኪዎችን ለማፍራትና በታችኛው የዕድሜ ክልል የሚገኙ ታዳጊዎችን አቅም ለማሳደግ ሥልጠናው ሙያዊ ግንዛቤን የሚፈጥር ነው፡፡

የዩኒቨርሲቲው ስፖርት አካዳሚ ለአካባቢው ማኅበረሰብ በተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች ሥልጠናዎችን እየሰጠ ሲሆን ይህንንም በተያዘለት ዕቅድ መሠረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል የአካዳሚው የክህሎት ሥልጠና ማዕከል አስተባባሪ አቶ በዛብህ አማረ ተናግረዋል፡፡

ሠልጣኞች በሰጡት አስተያየት በንድፈ-ሃሳብ እና በተግባር ያገኙትን እውቀት ወደ ውጤት በመለወጥ ተተኪ ታዳጊ የአትሌቲክስ ስፖርተኞችን የማፍራት ኃላፊነት የተጣለባቸው በመሆኑ በከፍተኛ ትኩረት የሚሠሩ መሆኑን ገልፀው ለተደረገላቸው ትብብር ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡