የሁሉ አቀፍ ሴክተር ዳይሬክቶሬት በሣውላ ከተማ አስተዳደር ከ1ኛና 2ኛ ደረጃ የመንግሥትና የግል ት/ቤቶች ርዕሳነ መ/ራን፣ የትምህርት ሥልጠና ቦርድ አባላት፣ የጤና ጽ/ቤት ኃላፊዎችና ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ጋር ወላጆቻቸውን በኤች አይ ቪ/ኤድስ ላጡ ህፃናት ሊደረግላቸው በሚገባ ድጋፍና እንክብካቤ  ላይ የካቲት 9/2009 ዓ/ም ውይይት አካሂዷል፡፡ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

 

የሁሉ አቀፍ ሴክተር ዳይሬክቶሬት የኤች አይ ቪ/ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ባለሙያ አቶ መርክነህ መኩሪያ እንደገለፁት የውይይቱ ዓላማ በኤች አይ ቪ/ኤድስ ዙሪያ ያለውን መዘናጋት በማስወገድ በሽታውን መከላከልና መቆጣጠር ብሎም ድጋፍና እንክብካቤ ለሚያስፈልጋቸው ትኩረት ለመስጠት የሚያስችል ግንዛቤ ማስጨበጥ ነው፡፡

አቶ መርክነህ ባቀረቡት የመወያያ ሰነድ እንደተመለከተው የቅንጅታዊ አሠራር እጥረት፣ ለወጣቶች የሚመጥን አገልግሎት አለመኖር፣ በሴክተር መሥሪያ ቤቶች የኤች አይ ቪ/ኤድስ ሜይንስትሪሚንግ ውይይቶች የተጠናከሩ አለመሆን፣ ፣ የጎዳና ተዳዳሪዎችና የሴተኛ አዳሪዎች መበራከት እንዲሁም የማታ ትምህርት፣ የምሽት ገበያዎችና መሠል ጉዳዮች የበሽታውን ሥርጭት የሚያባብሱ አጋላጭ ምክንያቶች ናቸው፡፡

የሣውላ ካምፓስ አስተባባሪ አቶ ገ/መድህን ጫሜኖ እንደተናገሩት የኤች አይ ቪ/ኤድስን ሥርጭት ለመግታት ተማሪዎች በበሽታው ላይ ያላቸውን ግንዛቤ እንዲያሳድጉ ዩኒቨርሲቲው በሥርዓተ ትምህርት አካቶ ትምህርት እየሰጠ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ለጎዳና ተዳዳሪዎችና ወላጆቻቸውን በቫይረሱ ላጡ ወገኖች የሚያደርገውን ድጋፍ በማስቀጠል ከባለድርሻ አካላት ጋር  ተቀናጅቶ ይሠራል ብለዋል፡፡

ተሳታፊዎች በአስተያየታቸው ከውይይቱ ያገኙት ግንዛቤ በቫይረሱ ላይ የተፈጠረውን መዘናጋት ለመቅረፍና ትኩረት ሰጥቶ የተሻሉ ተግባራት ለማከናወን የሚያስችላቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በውይይቱ ፍፃሜ ዩኒቨርሲቲው በሣውላ ከተማ ለሚገኙ 10 ወላጆቻቸውን በቫይረሱ ያጡ ህፃናት የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል፡፡