የትምህርት ጥራትና ሀገራዊ ህዳሴን የሚያረጋግጥ ብቁና ውጤታማ የትምህርት ማኅበረሰብ ለመፍጠር የጥልቅ ተሃድሶ መርሃግብር በዩኒቨርሲቲው ከየካቲት 27-መጋቢት 2/2009 ዓ.ም ድረስ ተካሂዷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

 

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደገለጹት የመርሃግብሩ ዓላማ የህዝብ አገልጋይነትና ውጤታማነትን የሚጎዱ የአስተሳሰብና የተግባር ዝንባሌዎችን በዲሞክራሲያዊ የሃሳብ ትግል በማስተካከል የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ የዲሞክራሲያዊ መንግስትን ባህሪያት ተረድቶ ለላቀ ፈፃሚነት እንዲነሳሳ ማድረግ ነው፡፡ በተጨማሪም በሀገራዊ የለውጥ ሂደት ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን የማረጋገጥ አቅጣጫ ላይ ግልፀኝነት እንዲዳብር በማድረግ በአመራሩና በሠራተኛው መካከል ጠንካራ መተማመንና መደጋገፍን ይፈጥራል ብለዋል፡፡

በተሃድሶ መድረኩ ‹‹ብቁና ውጤታማ መምህር፣ ተመራማሪና ፈፃሚ ለትምህርት ጥራትና ለሀገራዊ ህዳሴ!›› የሚል ሰነድ እና የዩኒቨርሲቲው የ2009 በጀት ዓመት የስድስት ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡ ባለፉት 15 ዓመታት በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ መስኮች የታዩ ለውጦችና ክፍተቶችን በመፈተሽ ለቀጣይ ሥራዎች የጋራ መግባባትን የሚፈጥሩ ጉዳዮች እንዲሁም በሀገር አቀፍ ደረጃ መንግስት ለትምህርት መስክ በሰጠው ትኩረት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚኖራቸው ድርሻና የሚጠበቀው ስኬት በስፋት ተዳሰዋል፡፡ የተሃድሶ መድረኩ በአስተዳደርና በአካዳሚክ ዘርፍ በአራት የኃይል መድረኮችና በበርካታ ቡድኖች ተከፋፍሎ ውይይት ተካሂዷል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ነጋሽ ዋጌሾ ውይይቱን ሲከፍቱ እንደተናገሩት በአመራሮች፣ በመምህራንና በሠራተኞች  መካከል የሚስተዋሉ ችግሮችን በመለየትና መልካም ግንኙነት እንዲፈጠር በማድረግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለአንድ ዓላማ መሳካት የበኩላቸውን ኃላፊነት ሊወጡ ይገባል፡፡ ስለሆነም በሥነ-ምግባር የታነፀና የሀገሪቱን ልማት የሚያፋጥን ዜጋን በማፍራት እና ከኪራይ ሰብሳቢነትና ከመልካም አስተዳደር ችግሮች የፀዳ ማኅበረሰብ በመፍጠር የትምህርት ጥራትን ማስጠበቅ ተቀዳሚ ተግባር አድርጎ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በንቅናቄ መድረኩ መምህራንና የአስተዳደርና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች የተሳተፉ ሲሆን የቀረበውን ሰነድ መነሻ በማድረግ በየመድረኩ ነፃ እና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ በርካታ ሀገራዊና ተቋማዊ ጉዳዮችን የሚመለከቱ ጥያቄዎችና ሃሳቦች ተነስተው በዩኒቨርሲቲው አመራሮችና የቦርድ አባላት ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡