ሰውኛ ኢንተርቴይመንት ከተለያዩ አጋር ተቋማት ጋር በመተባበር 121ኛውን የአድዋ ድል መታሰቢያ በዓል ከየካቲት 20-23/2009 ዓ/ም በተለያዩ ዝግጅቶች በአዲስ አበባ አክብሯል፡፡ በሰውኛ ኢንተርቴይመንት ግብዣ መሠረት ዩኒቨርሲቲያችን የአድዋ ጦርነትና ድሉን የሚዘክር ጥናታዊ ጽሑፍ በማቅረብና በተለያዩ ዝግጅቶች በመሳተፍ በመታሰቢያ በዓሉ ተካፍሏል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

በፕሮግራሙ አድዋን የሚዘክሩ የተለያዩ ኪነ-ጥበባዊ ኩነቶች የቀረቡ ሲሆን በአርባ ምንጭና አክሱም ዩኒቨርሲቲዎች የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍሎች፣ በኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን እንዲሁም በኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ የደራሼ የባህል ቡድን ጭፈራ የሆነው “ፊላ” እና ከአድዋ ጦርነት ጋር የተያያዙ ሽለላዎችና ፉከራዎችን በዘመናዊ መልክ በማዋሃድ በብዙዎች ዘንድ አድናቆት የተቸረው ትርዒት ለሁለት ተከታታይ ቀናት ቀርቧል፡፡

ዩኒቨርሲቲውን በመወከል በማህበራዊ ሣይንስና ሥነ-ሰብ ኮሌጅ ሥር ከሚገኙ ሦስት የት/ክፍሎች የተወጣጡ አምስት መምህራን እና የኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ተወካዮች ተሳታፊ የሆኑ ሲሆን በታሪክና ቅርስ አስተዳደር ት/ት ክፍል መምህር አቶ ዳንኤል ወርቁ ‹‹የዓድዋ ዘመቻ እና የኢትዮጵያዉያን ትብብር መገለጫዎች›› በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሁፍ ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡ በጥናታዊ ጽሁፉ በዓድዋ ጦርነት እና በጦርነቱ ጎልቶ የተንፀባረቀውን የኢትዮጵያ ህዝቦች አንድነት እና ትብብር ለማሳየት ተሞክሯል፡፡

በሀገራችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየደበዘዘ የመጣውን የማንነታችንና የአንድነታችን መገለጫ የሆነው የአድዋ ድል የአከባበር ሁኔታ በማጠናከር ለሰው ልጆች ክብር የተከፈለው መስዋዕትነት ሳይዘነጋ በምሉዕነት እንዲታወስ በማለም መታሰቢያ በዓሉ መዘጋጀቱን የሰውኛ ኢንተርቴይመንት ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ መዓዛ ታከለ ገልፀዋል፡፡ ፕሮግራሙ ድሉን ከመዘከር ባሻገር በሀገራችን ቀደምት ቱባ ጥበባት ላይ እሴት በመጨመር ከሀገር ውስጥ አልፎ ለዓለም ዓቀፍ ህብረተሰብ በተገቢው መንገድ እንዲተዋወቅ ለማድረግ ይረዳል፡፡

የፕሮግራሙ ተሳታፊዎች ስለ አድዋ ጦርነትና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው የተደረገ ሲሆን አድዋ እንደ መስህብና እንደ ማንነት በትውልዱ ላይ መልማት እንዳለበት የሚያወሱ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ቀርበው ሰፊ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡ በበዓሉ አከባበር ፍፃሜም ከምኒልክ አደባባይ እስከ አድዋ ድልድይ በተለያዩ የጎዳና ላይ ትርዒቶች እና በአርበኞች አለባበስ የታጀበ የእግር ጉዞ ተደርጓል፡፡ በማስቀጠልም እንጦጦ በሚገኘው የአፄ ምኒሊክ ቤተመንግሥት የታሪካዊ ቅርስ ጉብኝትና የጦርነቱን ዘመቻ የሚያሳይ ትውፊታዊ ተውኔት ለታዳሚው ቀርቧል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የደራሼ ባህላዊ የሙዚቃ ቡድን የፊላ ጨዋታን በአዲስ አበባ እቴጌ ጣይቱ ሆቴል እንዲያቀርብ በማጓጓዙና በማስተባበሩ በአዘጋጆቹና በበአሉ ታዳሚያን ልዩ ዕውቅናና አድናቆት ተችሮታል፡፡ በቀጣይም ሰውኛ ኢንተርቴይመንት በኪነ-ጥበብ ዘርፍ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በጥምረት ለመሥራት ከፍተኛ ፍላጎት እና ዕቅድ እንዳለው አዘጋጁ አርቲስት ሚኪያስ ሚሊዮን ገልጿል፡፡ በተጨማሪም የተጀመረው ግንኙነት እንደሚጠናከር የገለጸ ሲሆን በባህል፣ ታሪክና ተፈጥሮ ጉዳዮች የምርምርና ዶክመንቴሽን ሥራዎችን ለመሥራት የጋራ ስምምነት ሰነድ ንድፍ መዘጋጀቱን አሳውቋል፡፡

የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ኢትዮጵያዊያን ወራሪውን የጣሊያን ጦር ድል የነሱበት ታሪካዊ ቀን ሲሆን በወቅቱ የነበረውን ፍጹም የነጭ የበላይነት አስተሳሰብ በመስበር "የእንችላለን፤ እናሸንፋለን" መንፈስን ያላበሰ በመሆኑ የመላው ጥቁር ህዝብ ድል ተደርጎ ይወሰዳል። ጀግኖች አባቶቻችን ህይወታቸውን በመሰዋት ድል የተቀዳጁበትን 121ኛ የአድዋ የድል በዓል ‹‹የአድዋ ድል ብዝሃነትን ላከበረች ኢትዮጵያ ድህነትን ለማሸነፍ የሚያስችል ህያው አብነት›› በሚል መሪ ቃል በመላ ሀገሪቱ በድምቀት ተከብሯል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት