Print

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ብራይት ፊውቸር አግሪካልቸር ፕሮጀክት /BFA/ ‹‹የሥራ ፈጠራ ክሂሎትን ማሳደግ›› በሚል ርዕስ ከተለያዩ ክልሎች የግብርና እና ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኮሌጆች ለተወጣጡ መምህራን ከመጋቢት 23/2013 ዓ/ም ጀምሮ ለተከታታይ 8 ቀናት የአሠልጣኞች ሥልጠና ሰጥቷል፡፡

የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶ/ር ይስሃቅ ከቸሮ እንደተናገሩት ሠልጣኞች በራሳቸው ዘርፍ ሥራ እንዲፈጥሩና ለተማሪዎቻቸውም ማሳየት እንዲችሉ ክሂሎታቸውን ለማሳደግ የተዘጋጀ ሥልጠና ነው፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የሥልጠናው አስተባባሪና አሠልጣኝ አቶ ዱጋሣ ተሰማ በተለይ ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማትን የሚያሰለጥኑት የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኮሌጅ መምህራን በመሆናቸው አቅማቸውን ለመገንባትና ውጤታማ የሥራ ዕድል ፈጠራ ዕውቀት ማስተላለፍ እንዲችሉ ለማገዝ ሥልጠናው መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

ከኮምቦልቻ ግብርና ኮሌጅ የመጡት ሠልጣኝ ዶ/ር ናቤክ ተባሳ ሥልጠናው የመንግሥት ሥራ ጠባቂነትን ለማስቀረት በመምህሩ ብሎም በተማሪዎች ላይ የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት የሚረዳ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በኮሌጃቸው ኢንተርፕሪነርሺፕ ኮርስ በተግባር ተደግፎ የሚሰጥ መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ናብኪ ሥልጠናው ቀጣይነት ቢኖረው ለተማሪዎች አቅም የሚገነባ ነው ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ እንደገለጹት በአብዛኛው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የተዋቀረው በግብርናው መስክ ሲሆን በቀጣይ 10 ዓመታትም እንደ ሀገር ልዩ ትኩረት ከተሰጠባቸው 5ቱ የእድገት አቅጣጫዎች አንዱ የግብርናውን ዘርፍ ማዘመን ነው፡፡ ለዚህም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኮሌጆችና ኢንደስትሪዎች ትስስር ፈጥረው ከፍተኛ ድርሻ ማበርከት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በዚህ ረገድ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በብራይት ፊውቸር አግሪካልቸር ፕሮጀክትም ሆነ በሌሎች ዘርፎች ጠንካራ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል ያሉት ም/ፕሬዝደንቱ ሥልጠናው የሥራ ዕድል ፈጠራ ክሂሎትን መምህራን ለተማሪዎቻቸው ማስተላለፍ እንዲችሉ ትልቅ እገዛ ያደርጋል ብለዋል፡፡

በሥልጠናው ከመራዊ፣ ኮምቦልቻ፣ ቢሾፍቱ፣ አላጌ፣ ወላይታ፣ ወረታና ባኮ የግብርና እና ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኮሌጆችና ከዩኒቨርሲቲው የተወጣጡ 34 የሙያው ተቀራራቢ ልምድ ያላቸው መምህራን ተሳትፈዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት