Print

የዩኒቨርሲቲው ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት በዓለም ለ110ኛ በኢትዮጵያ ለ45ኛ ጊዜ የተከበረውን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ‹‹የሴቶችን መብት የሚያከብር ማኅበረሰብ እንገንባ›› በሚል መሪ ቃል መጋቢት 30/2013 ዓ/ም በሳውላ ካምፓስ አክብሯል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሪት ሠናይት ሳህሌ እንደገለጹት ማኅበረሰቡ በሴት ልጅ ላይ የፈጠረው የአመለካከት ችግር ሴቶች በራሳቸው እንዳይተማመኑ የሚያደርግ ነው፡፡ ይህንን የአመለካከት ችግር መቅረፍና ሴቶች በሴትነታቸው ምክንያት በትምህርታቸውና በሥራቸው የሚያጋጥሟቸውን ፆታዊ እንቅፋቶች በማስወገድ ምቹ ሁኔታ መፍጠር አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ሴቶች በብቃታቸው በአገሪቱ ቁልፍ ቦታዎች በኃላፊነት መምራታቸውና በተሰማሩበት መስክ የጎላ ለውጥ እያስመዘገቡ መሆኑ ለሌሎች ሴቶች መነሳሳትን የሚፈጥር መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በም/ፕሬዝደንት ማዕረግ የሳውላ ካምፓስ ዲን አቶ ገ/መድኅን ጫሜኖ ሴቶች አቅማቸውን በመጠቀም ብቁ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ጠንክረው ሊሠሩ ይገባል ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ታደለ ሸዋ ባቀረቡት ሰነድ እንዳብራሩት ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን የሚከበርበት ዋና ዓላማ በዓለም ያሉ መንግሥታት የሴቶች ጉዳይ የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የዲሞክራሲ ጉዳይ እንደሆነ አምነው በመቀበል በሴቶች ዙሪያ ፓሊሲዎቻቸውን፣ ሕጎቻቸውንና አሠራሮቻቸውን በመፈተሽ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ መድልኦዎችን እንዲያስወግዱና የሴቶችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት እንዲያረጋግጡ ለማነሳሳት ነው፡፡ በዓለም ላይ ያሉ ሴቶች በድንበር፣ በሃይማኖት፣ በቀለም፣ በቋንቋ፣ በባህል ወዘተ ሳይለያዩ የሚደርስባቸውን ጭቆናና መድልኦ የሚያወግዙበት፣ አንድነታቸውን የሚያጠናክሩበት፣ ድምጻቸውን በጋራ የሚያሰሙበት፣ ለነጻነት፣ ለፍትህና ለእኩልነት ያደረጉትን ተጋድሎ የሚዘክሩበት፣ ልምድ የሚለዋወጡበትና ለበለጠ ትግል ተቀናጅተው ለመንቀሳቀስ ቃል የሚገቡበትም ነው ብለዋል፡፡

በተመሳሳይም ‹‹በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ባለመታገስ የብልጽግና ጉዞን እናረጋግጥ›› በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ሰነድ በፕሬዝደንት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ገዝሙ ቀልቦ ቀርቦ ውይይት ተካሂዷል፡፡

በ2011 ዓ/ም 2ኛ ሴሚስተርና 2012 ዓ/ም የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ የሳውላ ካምፓስ ሴት ተማሪዎች በፕሮግራሙ የዕውቅና ሰርተፊኬት የተሰጠ ሲሆን የስኬት ተሞክሯቸውን ለተማሪዎች አካፍለዋል፡፡ በተጨማሪም ተማሪ እድላዊት በረከት ከምግብ ምኅንድስና ት/ክፍል 4.00 እና 17 A+፣ ተማሪ ገብርኤላ ሀብታሙ ከምግብ ምኅንድስና ት/ክፍል 4.00 እና 7A+፣ ተማሪ እፀገነት ቶላ ከቢዝነስ አድሚንስትሬሽን ት/ክፍል 4.00 እና 7A+ እንዲሁም ተማሪ ሰላማዊት ወርቄ ከሚዲያ ኮሚዩኒኬሽንና ፐብሊክ ሪሌሽን ት/ክፍል 4.00 እና 5 A+ በማምጣት ልዩ ስጦታ ተበርክቶላቸዋል፡፡

ተማሪ እድላዊት በረከት ጊዜዋን በአግባቡ በማከፋፈል ተጠቅማ በርትታ በመሥራቷ ለስኬት መብቃትዋን ተናግራለች፡፡ ዛሬን ተግቶ መሥራት ለነገ ማንነታችን መሠረት በመሆኑ መጪው ጊዜያችን መልካም እንዲሆን ዛሬን ጠንክረን መገኘት አለብንም ብላለች፡፡

ተማሪ ገብርኤላ ሀብታሙ በበኩሏ ጊዜን በአግባቡ መጠቀምና ውጤታማ የአጠናን ዘዴ አስፈላጊ መሆኑን ገልጻለች፡፡ የአቅም ማነስ፣ የሥነ-ልቦና ችግሮችና ሌሎችም ነገሮች የሚገጥሟቸውን ተማሪዎች ለማገዝ ካምፓሱ የሥነ-ልቦና ባለሙያ ቢኖረው መልካም እንደሆነም አስተያየቷን ሰጥታለች፡፡ በተጨማሪም የሴቶች ቀን መከበሩ የሚያስደስትና የሚያነቃቃ መሆኑንና ሴቶች የታመቀ አቅማቸውን አውጥተው እንዲጠቀሙ መልዕክቷን አስተላልፋለች፡፡

በፕሮግራሙ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ጽ/ቤት ኃላፊ፣ የካምፓሱ ዲን፣ ዳይሬክተሮች፣ መምህራን፣ ሴት ሠራተኞችና ተማሪዎች ተሳትፈዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት