Print

ኢሳት ቴሌቪዥን ከመጋቢት 20/2013 ዓ/ም ጀምሮ “ጎልጉል” በተሰኘ ፕሮግራሙ ለተከታታይ አራት ሳምንታት የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲን ገጽታ በከፍተኛ ሁኔታ ሊያጎድፍ የሚችል መረጃ ማሰራጨቱ ይታወሳል፡፡ የቴሌቪዥን ጣቢያው ከሚዲያና ከጋዜጠኝነት ሥነ-ምግባር ውጪ ዓላማውና ተልዕኮው ግልጽ ባልሆነ ሁኔታ ወቅታዊ ያልሆነና በተጨባጭም ለአሁናዊው ተቋማዊና አገራዊ ሁኔታ የማይመጥን፣ ለዩኒቨርሲቲውና ለአካባቢው ማኅበረሰብ፣ ለዩኒቨርሲቲው የቀድሞ ምሩቃን እንዲሁም ለዩኒቨርሲቲው ወዳጆችና ደጋፊዎች ሁሉ አሳዛኝ የሆነና የተጋነነ ፕሮግራም አሰራጭቷል፡፡ በፕሮግራሙ ላይ ሚዲያው ወገንተኛ፣ ብይን ሰጭና ፈራጅ የነበረ በመሆኑ እንዲሁም አንዳንድ የዩኒቨርሲቲው የቀድሞና የአሁን ኃላፊዎች የሰጡት አስተያየት ብዥታ የፈጠረ ስለሆነ በጉዳዩ ላይ ሚዛናዊና ወቅታዊ መረጃ መስጠት አስፈልጓል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የመንግሥት ተቋም ነው፡፡ የሕዝብ ሀብትም ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከ29,000 በላይ ተማሪዎችን በ6 ካምፓሶች ከ1ኛ - 3ኛ ዲግሪ በማስተማር ላይ እንደመሆኑ ከአቅርቦት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች፡- የተማሪዎች ቀለብ፣ የመብራት፣ የውሃ፣ የኢንተርኔትና ሌሎችም አገልግሎቶች በእርግጥም ጊዜ የማይሰጡና አንዱ እንኳን ቢጎድል በመማር ማስተማር ላይ ከፍተኛ ጫና ሊያሳድሩ የሚችሉ ከመሆናቸው መሰል ችግሮች በአፋጣኝ እንዲፈቱ ሲደረግም ሆነ በሌሎች ምክንያቶች አንዳንድ የአሠራር ስህተቶች መከሰታቸው በሁሉም ተቋማት የተለመደ ነው፡፡ ስለዚህም ነው የኦዲትና ኢንስፔክሽን ዘርፍ በተቋምና በፌዴራል ደረጃ ተቋቁሞ ሁሌም የግዥ፣ የፋይናንስ ክፍያ አፈፃፀም፣ የንብረት አያያዝና አስተዳደር እንዲሁም የአዋጆች፣ መመሪያዎችና ደንቦች አተገባበር በአግባቡ መፈጸሙን ቁጥጥር የሚያደርገው፡፡ የአሠራር ጥሰት የታየባቸው ጉዳዮችም የኦዲት ግኝት እየሆኑ ለሚመለከተው የበላይ አመራር ሪፖርት እየቀረበ ማስተካከያ መደረጉ የተለመደ አሠራር ነው፡፡ በዚህም መሠረት ከ2009 ዓ/ም - 2010 ዓ/ም ድረስ ታዩ የተባሉት የአሠራር ጥሰቶች እርምት እንዲደረግ ከዩኒቨርሲቲው የውስጥ ኦዲትና ከፌዴራል ኦዲት እንዲሁም ከሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት በተሰጠው ሪፖርት መሠረት እርምጃ ተወስዷል፤ እየተወሰደም ይገኛል፡፡ አንዳንዶቹ ጉዳዮችም በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በሂደት ላይ ያሉ መሆናቸውን ለማሳወቅ እንወዳለን፡፡

በእያንዳንዱ በጀት ዓመት በተቋማት የውስጥና የፌዴራል ኦዲተር የፋይናንስ፣ የግዥና ክዋኔ ኦዲት የተከሰቱ የአሠራር ክፍተቶች እንዲታረሙና የተፈፀሙ ጥፋቶች እርምጃ እንዲወሰድባቸው በሚቀርበዉ የኦዲት ሪፖርት መሠረት ማስተካከያ እርምጃ መውሰድ ያለና የሚኖር የአሠራር ሥርዓት ነው፡፡ በዚህ ሥርዓት መሠረት አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲም በየዓመቱ የውስጥና የፈዴራል ኦዲተር የሚያወጣቸውን የኦዲት ግኝቶችን መሠረት በማድረግ እርምጃ መወሰድ ባለባቸዉ ጉዳዮች ላይ የእርምት እርምጃዎችን ሲወስድ ቆይቷል፤ እየወሰደም ይገኛል፤ ወደ ፊትም በተመሳሳይ ሁኔታ ይቀጥላል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በእርግጥ በቅንነት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ለተማሪዎቻቸውና ለሕዝባቸው ሲሉ እንቅልፍ አልባ ሌሊቶችና እረፍት አልባ ቀናትን እየኖሩ ለሚያገለግሉ ምሁራን፣ ተመራማሪዎችና ሠራተኞች ታላቅ ክብርና አድናቆት አለው፡፡ በሀገርና ከሀገር ውጪ ሆናችሁ ለቀድሞ ተቋማችሁና ለአካባቢው ማኅበረሰብ በአቅማችሁ የምትችሉትን ሁሉ እያበረከታችሁ ለምትገኙ አምባሳደሮች በሙሉ ዩኒቨርሲቲያችን ሁሌም ከጎናችሁ ነው፡፡ ፈጽሞ በእንደዚህ ዓይነት ወራዳ ተግባርና የሥነ-ምግባር ዝቅጠት ላይ እንደማይገኝ እናረጋግጣለን፡፡

በአንዳንድ የቀድሞ የዩኒቨርሲቲያችን ሠራተኞች በነበሩ ግለሰቦች አማካኝነት በኢሳት ቴሌቪዥን መነጋገሪያ የሆነው ፕሮግራም የተቋሙን ክብርና ዝና በማጉደፍ በተቋሙ ላይ ጥርጣሬና ብዥታ የፈጠረ ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው፡፡

ይህንንም እኩይ ተግባር ዩኒቨርሲቲያችን በጽኑ ያወግዛል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ብዙዎቻችሁ የዩኒቨርሲቲያችን ማኅበረሰብና የቀድሞ አልሙናይ እንዲሁም ወዳጆቻችን ሁሉ የተሰራጨው መረጃ እውነተኛና ሚዛናዊ መስሏችሁ እጅጉን ልትሸማቀቁና ልታዝኑበት እንደምትችሉ እናስባለን፡፡ ስለዚህም ተገቢ ባይሆንም እውነታውን ይፋ ለማድረግ ያህል እነሆ ለዚህ ሁሉ ነገር ዋና ምክንያት የሆኑትን የወቅቱን ቦርድ ሰብሳቢ ግለ-ታሪክ እንነግራችኋለን፡፡

የወቅቱ ቦርድ ሰብሳቢ እስከ 2009 ዓ.ም ድረስ በዩኒቨርሲቲው በቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት መምህርና የሳይንቲፊክ ዳይሬክተርነትን ጨምሮ በአንዳንድ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ሲሠሩ የነበሩ ሲሆን በራሳቸዉ ጥፋት የተነሳ የዩኒቨርሲቲውን አመራሮች በማኩረፍ በ2009 ዓ.ም ዩኒቨርሲቲውን ለቀዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ያስተማረበትን ውል ሳይጨርሱ ሲለቁ ሲያስተምሩ የነበሩትን የ Post Graduate ተማሪዎች መንገድ ላይ ጥለው ሄደዋል፡፡

የወቅቱ የቦርድ ሰብሳቢ ዩኒቨርሲቲውን ለመልቀቅ እንዲፈቀድላቸው የተማሩበት የትምህርት ውል ግዴታ መጠናቀቅና ተማሪዎቻቸውን ማስጨረስ የሚጠበቅባቸው ስለነበር በመመሪያና ደንብ መሠረት የመልቀቅ ጥያቄያቸው ሊፈጸም የማይቻል በመሆኑ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች መመሪያና ደንብን ጥሰው ፍላጎታቸውን እንደማያሳኩ ሲገነዘቡ የሚፈልጉትን ጥቅም በሌላ መንገድ እንደሚያሳኩ በመግለጽ ከዩኒቨርሲቲው ሄደዋል፡፡

የወቅቱ ቦርድ ሰብሳቢ በመቀጠል ከሁለት ሳምንታት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥም የደ/ብ/ብ/ሕ/ክ/መ/ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ልማት ቢሮ ኃላፊ ሆነው የተሾሙበትን ደብዳቤ ይዘው መጡ፡፡ እጅግ በጣም በሚገርምና ድራማ በሚመስል ሁኔታና እስከ አሁንም እንዴት እንደተፈጸመ ግልጽ ባልሆነ መንገድ ከዩኒቨርሲቲው በለቀቁ ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ራሳቸውን የዩኒቨርሲቲው ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አስደርገዉ ተመድበው መጥተዋል፡፡ ይህ የመጀመሪያው ስህተት ነው፡፡ ከዩኒቨርሲቲው ጋር ተኳርፎ ለሄደ አንድ ግለሰብ የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢነት ኃላፊነት መሰጠቱ በራሱ ለዩኒቨርሲቲው ጥቅም እንዳልሆነ ግልፅ ነው፡፡ ይህንንም የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ መምህራንና ሠራተኞች በይፋ የሚያውቁት ሀቅ ነው፡፡ በቦርድ ሰብሳቢነት እንደተመደቡም አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በዩኒቨርሲቲው የሥነ-ምግባር ችግር ያለባቸውን የተወሰኑ ግለሰቦች በማሰማራት የዩኒቨርሲቲው አመራሮች የሚሠሩትን ሥራ ሁሉ ስህተት በሚያስመስል ሁኔታ አመራሮቹ የሚፈርሟቸው ደብዳቤዎች ሁሉ ኮፒ እየተደረጉ እርሳቸው ወደሚሠሩበት ቢሮ እንዲላክ አድርገው ሲያሠሩ ቆይተዋል፡፡ ይህም ከፍተኛ የሆነ ተቋማዊ አሠራርን የሚፃረር የሙያና ኃላፊነት ሥነ-ምግባር ችግር ነው፡፡

በዚህ ዓይነት የስህተት ፍለጋ ውስጥ ባሉበት በወንበር ግዥ ሂደት ላይ የተከሰተን የደብዳቤ አጻጻፍ ስህተት እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም ዩኒቨርሲቲው 43 ሚሊየን ብር ተዘርፏል የሚል ዘመቻ በማኅበራዊ ሚዲያ ተከፈተ፡፡ ይህም ያላረካቸው መሆኑን ሲያረጋግጡ ኢሳት ቴሌቪዥንን በመጠቀም ስለዩኒቨርሲቲው እጅግ የተዛባ መረጃ ሰጥተዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በአንዳንድ የሥራ ክፍሎች የተፈጸሙ የአሠራር ስህተቶችን በራሱ ለይቶ እርምጃ ወስዶ የተስተካከሉም ሆነ ሂደት ላይ ያሉ ጉዳዮችን ወቅታዊ ምጃ ሳይኖራቸው በ2009 እና በ2010 ዓ/ም ላይ ጅምር አካባቢ በነበሩ መረጃዎች ላይ ብቻ ተመስርተው አስተያየትና ገለፃ መስጠታቸው ከሚዲያ ሥነ-ምግባር አንጻር ተገቢ አይደለም፡፡ የቦርዱ ሰብሳቢ በዩኒቨርሲቲው እየሠሩ ባሉበት ጊዜ በተፈጠረው አለመግባባት በዩኒቨርሲቲው ላይ በያዙት ኩርፍያና አለፍ ሲልም ጠንከር ያለ ቂም ተቋሙን ለመጉዳት አስበው እየሠሩ እንደነበር ከሰብሳቢው ጋር የተመደቡት ሌሎች የቦርድ አባላት ግንዛቤው ስላልነበራቸው እርሳቸው የዩኒቨርሲቲው የቀድሞ መምህርና ኃላፊም ከመሆናቸው ጋር ሌሎቹን የቦርድ አባላት ይሁንታ ለማግኘት ከፍተኛ ጫና የማድረግ ዕድል በመጠቀም ዓላማቸውን ለማሳካት ስውር እርምጃዎችን ሄደዋል፡፡

በ2010 ዓ.ም መጨረሻ ላይ በዩኒቨርሲቲው የ2010 በጀት ዓመት ሥራ አፈጻጸም ሪፖርትና በ2011 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ የዩኒቨርሲቲዉ ሥራ አመራር ቦርድና የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራር በጋራ ግምገማ ሲያካሂዱ አንድ የቦርድ አባል “ለመሆኑ በናንተ በከፍተኛ አመራር መካከል የጋራ መግባባት አለ?” የሚል ጥያቄ አነሱ፡፡ ፕሬዝደንቱም " አዎን የመግባባት ክፍተት አለ፤ የችግሩ ዋና ምክንያት ግን የቦርዱ ሰብሳቢ ነው፡፡ የወቅቱ ቦርድ ሰብሳቢ በአመራሩ መካከል የራሳቸውን ቡድን በማደራጀት ሌሎቹን አመራሮች ለማጥቃት እየሠሩ ስለሚገኙ ነው" በማለት መልስ ሰጡ፡፡ ሌላው የቦርድ አባልም እንደመደንገጥና ግራ እንደ መጋባት ብለው ሌላ ጥያቄ “ይህ ከሆነ ታዲያ መጀመሪያ የቦርዱ ሰብሳቢ ሲመደብ ለምን ለሚመለከተዉ አካል አላሳወቅህም?" ሲሉ ፕሬዝደንቱን በድጋሚ ጠየቁ፡፡ ፕሬዝደንቱም "በስልክና በቃል አሳውቄያለሁ፤ ነገር ግን የቦርዱ ሰብሳቢ ቀጥሎ የሚያሳየዉን ባህሪ ተከታተል እንጂ ያለፈውን እርሳው" የሚል ምላሽ ከላይ እንደተሰጣቸው ለቦርዱ አባል መለሱ፡፡

በሚቀጥለው ቀን ጠዋት ቦርዱ የራሱን የብቻ ስብሰባ በማድረግ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ከኃላፊነት እንዲነሳ ለትምህርት ሚኒስቴር ለማቅረብ ወሰነ፡፡ በዚያው ቀን ከሰዓት በኋላ በዩኒቨርሲቲው ችግር አለ ተብሎ በቀረበው ሪፖርት ላይ ከዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ጋር ለመወያየት ከትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ፣ የዩኒቨርሲቲዉ ቦርድ አባላት፣ የዩኒቨርሲቲው ካውንስል፣ በርካታ መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች ባሉበት በአዳራሽ የሁለት ቀናት ውይይት ተካሄደ፡፡

በውይይቱ መጨረሻም የተነሱ ጉዳዮችን እንደገና መረጃ አጠናቅሮና አጣርቶ የማስተካከያ እርምጃዎች እንዲወሰዱና በአመራሩ መካከል በቡድን መልክ የሚታየው አለመግባባት እንዲቆም አቅጣጫ በተሰጠው መሠረት በዩኒቨርሲቲው የተነሱ ጉዳዮችን በጋራ አጣርተው ያለውን መረጃ እንዲያቀርቡ የዩኒቨርሲቲው ሕግ አገልግሎት፣ የኦዲትና ኢንስፔክሽን እና የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሮች ተመድበው ባቀረቡት መረጃ መሠረት የማስተካከያ እርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ ሆኖም በወቅቱ የዚህ ኮሚቴ አባል የነበሩት የዩኒቨርሲቲው ኦዲትና ኢንስፔክሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር እንኳን የተቋሙን ትክክለኛ መረጃና የተፈጠሩ ስህተቶች የታረሙ መሆናቸውን በተመለከተ ተገቢውን መረጃ ሳይይዙ በሁሉም የስርጭቱ ክፍሎች አወዛጋቢና የተዛባ መረጃ ሲሰጡ ተመልክተናል፡፡ ይህም በተመልካች አድማጭ ላይ ከፍተኛ ብዥታ የመፍጠር ሚና የነበረው ነው፡፡

ኢሳት ቴሌቪዥን መረጃ ሳያጣራ ተፈጠረ የተባለውን ሙስና፣ የሀብት ዝርፍያና ምዝበራ አስመልክቶ በተቋሙ ላይ እርምጃ የሚወስድ አካል የሌለ በማስመሰል፣ ተቋሙ የመንግሥት አሠራር እንደማይከተል፣ ሃይ ባይ አካል እንደሌለው አድርጎ በመፈረጅና የመንግሥት መዋቅር መሆኑንም በመዘንጋት እንዲሁም አሁን ላይ ካሉት የቦርድ አባላት፣ ከፍተኛ አመራሮችና ሌሎች ስለጉዳዮቹ ቅርብ ከሆኑ ዘርፎች በተገቢ ሁኔታ ሚዘናዊ መረጃ ሳያጠናቀር፣ ለሚከታተለው ሕዝብ የሚያስተላልፈውን መረጃ በቅጡ ሳይመረምርና ከሦስትና አራት ዓመታት በፊት የነበሩ ጉዳዮች በአሁኑ ወቅት ያሉበትን ደረጃ ሳያጣራና ሳያረጋግጥ ወቅታዊ ያልሆነ መረጃ ወገንተኝነት፣ ብይን ሰጪነትና ፍረጃ በተሞላበት ሁኔታ የተዛባና ኢ-ሚዛናዊ መረጃ ማሰራጨቱ ከአንድ የሕዝብ አገልጋይ ነኝ ከሚል ሚዲያ የማይጠበቅና ሙያዊ ሥነ-ምግባር የሚፃረር ተግባር ነው፡፡

ኢሳት ቴሌቪዥን ተፈጥረው እርምጃ አልተወሰደባቸውም ያላቸውን ጉዳዮች፡- የአዳራሽ ወንበር ግዥ፣ የነዳጅ ማደያ ግንባታ፣ የመኪና ግዥ፣ የብረት መቁረጫ ግዥ፣ የጄኔሬተርና የጄኔሬተር ገመድ ግዥ፣ የውሎ አበልና የትርፍ ሰዓት ክፍያ፣

የጋራዥ አጥር ግንባታ፣ የመስተንግዶ አገልግሎት ክፍያ፣ የውሃና ኤሌክትሪክ ጥገና ዕቃዎች ግዥና አሠራሮችን በተመለከተ ለመላው ሕዝብ ባሉት የሚዲያ አማራጮች ሁሉ በተከታታይ ሚዛናዊ መረጃ እንዲቀርብ የሚደረግ መሆኑን እናሳውቃለን፡፡

በተነሱት ጉዳዮች አጠር ያለ መረጃ ለጊዜው ለመስጠት ያህል "43 ሚሊዮን ተዘርፏል" እየተባለ በማኅበራዊ ሚዲያና በቴሌቪዥን ጣቢያው አጀንዳ የተደረገው የአዳራሽ ወንበር ግዥ ጉዳይ ለድርጅቱ በቅድመ ክፍያ ከተከፈለው ውጪ ምንም ዓይነት ክፍያ ያልተፈፀመ መሆኑና ድርጅቱ ያቀረበው ወንበር በግዥ መስፈርቱ መሠረት ጥራቱ በባለሙያ ተረጋግጦ ገቢ እንዲደረግ ሲጣራ ወንበሩ በግዥ መስፈርቱ መሠረት አለመቅረቡ መረጋገጡና ድርጅቱ ወንበሩን አራግፎ ከመሄዱም በላይ ዩኒቨርሲቲው በግድ እንዲቀበለው ጫና የመፍጠር ፍላጎት ያለው በመሆኑ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በክስ ሂደት ላይ ያለ መሆኑ፣ የነዳጅ ማዳያ ግንባታም በግንባታ ሥራዎች መመሪያና ደንብ መሠረት የተከናወነና በወቅቱም ቢሆን በተለየ ሁኔታ ምንም ዓይነት የዋጋ ግነት የሌለው መሆኑ፣ ከብረት መቁረጫ ግዥ ጋር "በፓኬት ተጠይቆ በነጠላ ሂሳብ ተከፍሎ ተገኘ" የተባለው ከቅድመ ክፍያ በኋላ ቀጣይ ክፍያ ሳይፈፀም የተፈጠረው ስህተት በመታወቁ ከቅድመ ክፍያው ላይ እላፊ የተከፈለው ገንዘብ ለዩኒቨርሲቲው ተመላሽ የተደረገ መሆኑና መታረሙ እንዲሁም የጄኔሬተርና የጄኔሬተር ገመድ ግዥ በተመለከተ "የገመዱ ዋጋ ከጄኔሬተሩ በለጠ" የተባለው ጉዳይም በወቅቱ ከአንድ ድርጅት በአጠቃላይ 6 ጄኔሬተሮች በጨረታ መገዛታቸውና ለሁሉም ጄኔሬተሮች አስፈላጊ የሆነ ተጨማሪ ገመድ የተገዛ መሆኑ እንጂ ለአንድ ጄኔሬተር ብቻ ያልተገዛ መሆኑና ምንም ዓይነት የግዥ አሠራር ችግር የሌለበት መሆኑ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በተጨማሪም የትርፍ ሰዓትና የውሎ አበል ክፍያ የተባለው ግኝቱ ሙሉ በሙሉ ተመላሽ ተደርጎ የተስተካከለ መሆኑ፣ ከጋራዥ አጥር ግንባታ ጋር በተያያዘም ማስተካከያ የተደረገ እና ጥፋቱን የፈፀሙ ግለሰቦች የተቀጡበትና የአጥሩ ግንባታ ስህተቱ ታርሞ የተሠራ መሆኑ፣ ''የምርምር አውደ ጥናት ተሳታፊዎች የመስተንግዶ አገልግሎት ክፍያ ዩኒቨርሲቲውን ለከፍተኛ ተጨማሪ ወጪ የዳረገ ነው'' የተባለው ዩኒቨርሲቲው ለሌሎች የተለያዩ ጉዳዮች የመጡ እንግዶች የአገልግሎት ክፍያ ጨምሮ ከፈለ እንጂ ምንም ዓይነት የአሠራር ስህተት የሌለው መሆኑ፣ የውሃና የኤሌክትሪክ ዕቃዎች ግዥም በወቅቱ የተስተካከለ መሆኑና "በኮንስትራክሽን ዘርፍ ከ6 ሕንፃ ተቋራጭ ድርጅቶች ጋር በመመሳጠር መኪና ተገዝቷል" የተባለውም በአሁኑ ሰዓት እንደ ተቋም ከፍተኛ የመኪና ዕጥረት ያለ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ለምርምርና ለመማር ማስተማር መሳለጥ የሚያግዙ ተጨማሪ መኪናዎች ለማሟላት ጥረት ቢያደርግም በግኝት ስለተለየ ወዲያው የተስተካከለና ከኮንትራት ውል እንዲወጣ በማድረግ ምንም ዓይነት የተገዛ መኪና አለመኖሩና ሌሎች አሠራሮችም በየጊዜው እንዲስተካከሉ ጥረት እየተደረገ እንደ ሀገር ካሉ ተቋማት ተጨባጭ ሥራዎችን እየሠራ በሚገኝበት ወቅት እንዲህ ዓይነቱ መሠረተ-ቢስ ውንጀላ ተገቢነት የሌለው መሆኑን በፅኑ እናስገነዝባለን፡፡ ከዚህ ሀቅ ውጪ ዩኒቨርሲቲው መመሪያና አሠራርን በመጣስ ምንም ዓይነት የመንግሥትና የሕዝብ ገንዘብ እንዲባክን አለማድረጉን መላው ማኅበረሰብ እንዲገነዘብ እንወዳለን፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በቅርብ ጊዜ እንኳን በጥፋታቸው ምክንያት የዲስፕሊን እርምጃ የተወሰደባቸው አንዳንድ ግለሰቦች በአሠራሩ መሠረት የቀድሞው ቦርድ ሰብሳቢ ከዩኒቨርሲቲው ቦርድ ሰብሳቢነት ከተነሱ ከሁለት ዓመታት በኋላም እንኳን ለተልዕኳቸው ማሳኪያ እንዲሆናቸው ወደ ቀድሞው የቦርድ ሰብሳቢ ዘንድ በመሄድ ተቋሙን ለመበቀል በማሰብ በኢሳት ቴሌቪዥን ተገቢ ባልሆነ ሁኔታ የዩኒቨርሲቲውን ገጽታ በሚያበላሽ ተግባር ላይ ተሳትፈዋል፡፡

በተለያዩ ምክንያቶች ዩኒቨርሲቲውን የለቀቁ የቀድሞ አመራሮችና ሌሎች አካላት ዩኒቨርሲቲው እየሠራ የሚገኘውን ሁኔታ በአግባቡ እየተገነዘቡ የተቋሙን ለማጉደፍ መሞከር ለተመልካቹ ሕዝብ ክብር አለመስጠትም ጭምር እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ዩኒቨርሲቲው የዲሲፕሊን ችግርን በተደጋጋሚ ይፈጥሩ የነበሩ አካላት ሁሉ በኢሳት ቴሌቪዥንና በማኅበራዊ ሚዲያዎች

በተቋሙ ላይ የከፈቱትንና እየከፈቱ የሚገኙትን የገጽታ ማጠልሸት ተግባራት አስመልክቶ በሕግ ተጠያቂነት እንዲኖር እየሠራ ይገኛል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በውኃና ሌሎችም የምኅንድስና ዘርፎች፣ በቴክኖሎጂ፣ በተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ፣ በማኅበራዊ ሳይንስና ስነሰብ፣ በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ፣ በሕክምናና ጤና ሳይንስ እንዲሁም በግብርና ሳይንስ ዘርፎች የሚሠራቸውን ተግባራት በምርምር ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራቱን የሚቀጥል መሆኑን በድጋሚ እያረጋገጠ ዩኒቨርሲቲው ከ30 ዓመታት በላይ የገነባውን ዝናና ክብር እንዲሁም የሕዝብ አመኔታ ለማስቀጠል ከመቼውም በላይየተሰጠውን ተልዕኮ ለማሳካት በትጋትና ታማኝነት ይፈፅማል፤ ያስተምራል፤ ይመራመራል እንዲሁም ማኅበረሰቡን በቅንነት ያገለግላል፡፡ ዩኒቨርሲቲያችን በአሁኑ ሰዓት በአገር ደረጃ የምርምር ዩኒቨርሲቲ ከተደረጉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አንዱ መሆኑና ከአቻ ተቋማት ተወዳዳሪ ተግባራትን እያከናወነ ስለመቆየቱ ይህ ልየታ ምስክር ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲያችን አሁንም ወደ ፊትም አንጋፋነቱን አስጠብቆ የምርምር ፋና ወጊ በመሆን የሀገራችን የውሃ ሃብት ልማትና አስተዳደር ምርምር፣ ትኩረት የሚሹ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች ምርምርና ሥልጠና፣ የታዳሽ ኃይል ምርምርና ስርፀት፣ የብዝሃ-ሕይወት ምርምርና ጥበቃ እንዲሁም የባህልና ቋንቋ ምርምር የልኅቀት ማዕከል ለመሆን እየተገ ነው፡፡

ለመላው የዩኒቨርሲቲያችንና አካባቢው ማኅበረሰብ፣ የዩኒቨርሲቲው ቀድሞ ምሩቃንና ወዳጆች፣ የዞኑና የፌዴራል መንግሥት ተቋማት የተዛባውን መረጃ በማጥራትና ሚዛናዊና ፍትሐዊ መረጃ በማሰራጨት የተቋማችንን ዝና እንድንጠብቅና በማኅበራዊ ሚዲያም ሆነ በተመሳሳይ ሁኔታ ኢሳት ቴሌቪዥን ባደረገው መልክ የሚደረግን ኃላፊነት የጎደለውን ተግባር በጋራ በመሆን በፅኑ እንድናወግዝ ዩኒቨርሲቲው ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የኢሳት ቴሌቪዥን የፈጸመው ተግባር ኃላፊነት የጎደለው የሚገባ ስለሆነ በይፋ ዩኒቨርሲቲውንና ተመልካቹን ይቅርታ እንዲጠይቅና በተዛባው መረጃ የተፈጠረውን ብዥታ በአስቸኳይ እንዲያጠራ እያሳሳብን ይህ ባይደረግ ግን የሚዲያ ተቋሙ በጥቅልና በቀረበው ዶክመንተሪ ላይ ድርሻ የነበራቸውን አካላት በሕግ አግባብ ተጠያቂ እንዲሆኑ የሚደረግ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ