Print

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በገረሴ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ነፃ የማሕፀን ውልቃት ቀዶ ጥገና አገልግሎት ሚያዝያ 19/2013 ዓ/ም ሰጥቷል፡፡

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የማሕፀንና ጽንስ ስፔሻሊስት ዶ/ር ነጋ ጩፋሞ ዩኒቨርሲቲው ትኩረት ሰጥቶ ከሚያከናውነው የመማር ማስተማር ሥራዎች ባሻገር በየዘርፉ የማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራዎችን እንደሚሠራ ተናግረው የማሕፀን ውልቃት በሽታ እየሰፋ ከመጣባቸው አካባቢዎች ገረሴና አካባቢው አንዱ በመሆኑን ጠቅሰው የገረሴ አጠቃላይ ሆስፒታል ዩኒቨርሲቲውን ትብብር በመጠየቁ አገልግሎቱ መሰጠቱን ጠቁመዋል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

እየተሰጠ የሚገኘው አገልግሎትም ታካሚዎች አርባ ምንጭና ወላይታ ሶዶ ድረስ በመሄድ የሚያባክኑትን ጊዜና ገንዘብ የሚያድን መሆኑንም ዶ/ር ነጋ ጠቁመዋል፡፡

የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ብርሃኑ ብርቄ ዩኒቨርሲቲው ከእናቶች ጤና ጋር በተያያዘ ለሆስፒታሉ እያደረገ ያለው አገልግሎት ሳይቋረጥ መቀጠሉ ሆስፒታሉ እንደ ደረጃውና እንደ አካባቢው ነባራዊ ሁኔታ አገልግሎቱን በበቂ ሁኔታ እንዳይሰጥ የሚያደርጉ ተግዳሮቶችን የሚፈታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እንደ ዶ/ር ብርሃኑ ገለጻ በተለይ ከወሊድ ጋር በተያያዘ የ ICU፣ የኦክስጅን እጥረትና መብራት በተፈለገው መልኩ አገልግሎት አለመስጠት፣ ጄኔሬተር ለመጠቀም ነዳጅ በበቂ ሁኔታ አለመቅረብና ሌሎችም በሆስፒታሉ ከሚከሰቱ የግብዓትና የቁሳቁስ ችግሮች መካከል መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ስለሆነም ዩኒቨርሲቲውም ሆነ ሌሎች ባለድርሻ አካላት በሆስፒታሉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የበኩላቸውን ድጋፍ ቢያደርጉ ሲሉ ዶ/ር ብርሃኑ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በቀጣይ ከ2 ሳምንት በኋላ የህክምና ቡድኑ በዚሁ ሆስፒታል ተገኝቶ ተመሳሳይ ህክምና እንደሚሰጥ የተገለፀ ሲሆን በመቀጠልም መሰል አገልግሎት በጊዶሌ፣ ካምባና ጨንቻ ለመስጠት መታቀዱ ተገልጿል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት