Print

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከጋሞ ዞን ትምህርት መምሪያ ጋር በመተባበር በዞኑ ከሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለተወጣጡ መምህራን በቤተ-ሙከራ አጠቃቀምና አተገባበር ዙሪያ ከሚያዝያ 26/2013 ዓ/ም ጀምሮ ለ5 ተከታተይ ቀናት የአሠልጣኞች ሥልጠና ሰጥቷል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ፈቃዱ ማሴቦ እንደገለጹት ጥራት ያለውን ትምህርት ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ መሰል ሥልጠናዎችን ማዘጋጀት ፋይዳው ጉልህ ነው፡፡ በተለይ በተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ዘርፍ በተግባር የተደገፈ ትምህርት ወሳኝ በመሆኑ ተማሪዎች እያንዳንዱን የቤተ-ሙከራ አጠቃቀም በተግባር እያዩ ውስን ግብዓቶችን በጥንቃቄ በመጠቀም ክሂሎታቸውን እንዲያዳብሩ የቤተ-ሙከራ መምህራንን ዕውቀት ማሻሻል ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡ እንደ ዶ/ር ፈቃዱ ተማሪው ከተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ሽሽት ወደ ሌሎች የማኅበራዊ ሳይንስ መስኮች ላይ ብቻ ትኩረት እንዳያደርግ ሥልጠናው ያግዛል፡፡

የኮሌጁ የማኅበረሰብ አገልግሎት አስተባባሪ ዶ/ር ተስፋዬ ገ/ማርያም በበኩላቸው ሥልጠናው ከ9ኛ - 12ኛ ክፍል ኬሚስትሪ፣ ባዮሎጂና ፊዚክስ ለሚያስተምሩ መምህራን ከቤተ-ሙከራ ጋር ያላቸውን ግንኙነት የሚያጠነክር ነው ብለዋል፡፡ የመማር ማስተማር ሂደት በተግባር በቤተ-ሙከራ የተደገፈ እንዲሆን ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚኖርባቸው አስተባባሪው ገልጸዋል፡፡

የጋሞ ዞን ትምህርት መምሪያ የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ዳይሬክቶሬት ቡድን መሪ አቶ ደረጀ እሸቱ እንዳሉት ባለፉት ዓመታት የተለያዩ አጋዥ ደንቦችንና መመሪያዎችን በማዘጋጀት የትምህርቱን ሥራ ለመደገፍ በርካታ ተግባራት ሲከናወኑ ቆይተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከመስክ እይታና ከሚቀርቡ ሪፖርቶች የሚስተዋለውን የትምህርት ጥራት ችግር በመገንዘብ የተቀናጀ የሳይንስ ትምህርት ማለትም የፊዚክስ፣ የኬሚስትሪና የባዮሎጂ ትምህርቶች ሳይንሳዊ ሙከራ የሚከናወንባቸው በመሆናቸው የቤተ-ሙከራ አያያዝና አደረጃጀት ሥልጠና መስጠት አስፈልጓል ብለዋል፡፡ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ማምጣት የሚቻለው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ትምህርቶችን በማሳደግ ስለሆነ ትምህርት ቤቶችን የወቅታዊ ቴክኖሎጂ ውጤቶች ተጠቃሚ ማድረግ ለትምህርት ጥራትና ተገቢነት መጠበቅና ለተማሪዎች ውጤት መሻሻል አስፈላጊ በመሆኑ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን አቶ ደረጀ ገልጸዋል፡፡

የጋሞ ዞን ትምህርት መምሪያ የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ዘርፍ የሥርዓተ-ትምህርት ባለሙያ ወ/ሮ መሰለች መስቀሌ እንደተናገሩት ሥልጠናው በዞኑ የሚገኙ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የቤተ-ሙከራ ባለሙያዎች የአሠልጣኞች ሥልጠና ያገኙበት በመሆኑ ይህም ተማሪዎች ከተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ዘርፍ እንዳይሸሹና በተግባር የተደገፈ ትምህርት እንዲያገኙ የሚያደርግ ነው፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት