6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ አስመልክቶ በትምህርት ጥራትና አግባብነት ዙሪያ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ፕሮፌሰሮች ካውንስልና ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የተፎካካሪ ፓርቲዎች የክርክር መድረክ ሰኔ 05/2013 ዓ/ም በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ሰለሞን ተሾመ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ የላኩትን መልዕክት በንባብ ሲያስደምጡ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን በተገኙበት በትምህርት ጥራትና አግባብነት ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲወያዩ መደረጉ ችግር ፈቺ የመፍትሄ ሃሳቦችን ለማግኘት እንደሚረዳና መሰል መድረኮች የሀገራችንን የፖለቲካ ባህል የማሳደግ ሚናቸው ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ መድረኩ ለምርጫ ብቻ ሳይሆን ከተለያየ ቦታ የተገኙና የተለያየ አስተሳሰብ ያላቸው ግለሰቦች ተገናኝተው የሀገሪቱ የትምህርት ዘርፍ የእስካሁኑ ጉዞና የወደፊት ዕጣ ፈንታው ምን መሆን እንዳለበት የዕውቀት ሽግግር የሚያከናውኑበት ነውም ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ትምህርት ለአንድ ሀገር እድገት ወሳኝ እንደመሆኑ የትምህርት ጥራት፣ አግባብነት፣ ተደራሽነትና ፍትሃዊነትን አስመልክቶ በልዩ ትኩረት መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ በቀጣይ መንግሥት ለመሆን እየተወዳደሩ ያሉ ፓርቲዎች የትምህርት ፖሊሲያቸውን ከማራመድ አኳያ የሚያቀርቡት ሃሳብ ለሀገራችን ሕዝብ በትምህርቱ መስክ ትልቁን ጥያቄ የሚመልስ በመሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች መወያየታቸው ፋይዳው የጎላ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

በመድረኩ ኢሶዴፓን ወክለው የቀረቡት አቶ ወንድሙ ቡቶ ፓርቲያቸው ሀገር የሚለማውና የሚለወጠው ሁሉም በሙሉ አቅሙ ከልቡ ሲሠራ መሆኑን እንደሚያምን ገልጸው ፓርቲያቸው መንግሥት የመመሥረቻ ድምጽ ቢያገኝ የሕዝቡን ታሪካዊ፣ ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሌሎችም እሴቶች ከግምት ያስገባ ሥርዓተ ትምህርት ያዘጋጃል ብለዋል፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ተወካዩ ረ/ፕ አንተነህ በልሁ የሀገርን ብልጽግና ለማረጋገጥ፣ ዕውቀትን ለማስፋፋትና የተጀመሩ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ ፓርቲያቸው ሰፊ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ ጠቅሰው ለወደፊቱም በአጠቃላይ ማኅበራዊ መስተጋብሮች በዕውቀት የተቃኙ እንዲሆኑና መስተካከል ያለባቸውን ጉዳዮች ለማረም እንተጋለን ብለዋል፡፡

የእናት ፓርቲ ተወካይ አቶ ሀ/ገብርኤል ቃይዳ ትምህርት የሰው ልጅ በሕይወት ዘመኑ ያጠራቀማቸውን በጎ እሴቶች ለቀጣዩ ትውልድ የሚያስተላልፍበት መሳሪያ መሆኑን ገልጸው ፓርቲያቸውም በክሂሎት፣ በአመለካከትና መሰል ነገሮች ትውልድ ይታነጻል የሚል እምነት እንዳለው ተናግረዋል፡፡ ስለሆነም ፓርቲያቸው በሥነ-ምግባር የተገነባ፣ ዕውቀትን አብዝቶ የሚሻ፣ ጠያቂ፣ ሞጋች፣ ተመራማሪና ፈጣሪ ትውልድ እንዲፈጠር ጠንክሮ እንደሚሠራ ጠቁመዋል፡፡

በክርክር መድረኩ ጥሪ ከተደረገላቸው 20 የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል 11ዱ ሲገኙ 2ቱ ለክርክሩ ራሳቸውን ባለማዘጋጀታቸው ክርክሩ በኢሶዴፓ፣ ብልጽግና፣ እናት፣ ባልደራስ፣ አዲስ ትውልድ፣ ኢዜማ፣ ነእፓ፣ ጋዴፓና ቁዴፓ መካከል የተከናወነ ሲሆን ከፓርቲዎቹ በቀረቡት ሃሳቦች መነሻነት ከትምህርት ጥራት ጋር የተያያዙ የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች በተሳታፊዎች ተነስተዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት