የዩኒቨርሲቲው የማኅበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ የማኅበረሰብ አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ለጨንቻ ወረዳ ሆሎኦ ላካ ሙሉ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት ሰኔ 3/2013 ዓ/ም የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል፡፡

የማኅበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ ም/ዲን አቶ ኤርሚያስ በፈቃዱ ዩኒቨርሲቲው በጨንቻ ወረዳ የእንሰት ፓርክ ሲያቋቁም ት/ቤቱ ከራሱ ይዞታ መሬት መስጠቱን አስታውሰው ት/ቤቱ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት ለመጀመሪያ ዙር ለመማር ማስተማር አጋዥ የጽሕፈት መሳሪያዎች ድጋፍ አድርገናል ብለዋል፡፡ ትምህርት ቤቱ በኢኮኖሚ ያላደገ በመሆኑ በማኅበረሰብ አገልግሎት ዕቅዳቸው ውስጥ አካተው መሰል ድጋፎችን ማድረግ እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የኮሌጁ የማኅበረሰብ አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ተወካይ አቶ አብዱራህማን ኡስማን ለት/ቤቱ የተደረገው ድጋፍ በተወሰነ ደረጃ የት/ቤቱን የግብዓት ችግር የሚቀርፍ መሆኑን ገልጸው በቀጣይ ክፍተታቸውን እያጤንን የምንችለውን ድጋፍ ሁሉ ለማድረግ እንሠራለን ብለዋል ፡፡

የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህርት ወ/ሮ ገነት አስረስ እንደገለጹት በትምህርት ቤቱ የመማር ማስተማር ሥራዎችን ለማካሄድ የጽሕፈት መሳሪያ ችግሮች በሰፊው የሚስተዋሉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የተገኘው ድጋፍ የግብዓት ችግሮችን በመቅረፍ የመምህራን የሙያ ማሻሻያ ሥልጠናዎችን፣ ጥናትና ምርምሮችን፣ የመጽሐፍ ግምገማዎችንና በአጠቃላይ የትምህርት ሥራዎችን ለማካሄድ ይረዳናል ብለዋል፡፡ ርዕሰ መምህርቷ ለተደረገላቸው ድጋፍ ምስጋና አቅርበው በቀጣይም የት/ቤቱ ማኅበረሰብና አመራር አካላት ከዩኒቨርሲቲው ጋር ትስስር በመፍጠር ት/ቤቱን ለማሻሻል በትኩረት እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት