በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አዘጋጅነት ‹‹ድምጻችን ለነፃነታችንና ለሉዓላዊነታችን›› በሚል መሪ ቃል አገር አቀፍ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች በጋራ ድምጽ የሚያሰሙበት የበይነ-መረብ መርሃ-ግብር ሰኔ 3/2013 ዓ.ም ተካሂዷል፡፡ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም በፕሮግራሙ ተሳትፈዋል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ በድሩ ሂሪጎ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያዊነታችን መገለጫና የአገር አንድነት ማሳያ በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በግድቡ ዙሪያ አንድ አቋም መያዝ አለበት ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በውሃ ዘርፍ በርካታ ምሁራንና የሚዲያ አካላትን እየጋበዘ አገራዊ ጉባዔ በማዘጋጀት ስለ ግድቡ ጥልቅ ዕውቀት ለማስጨበጥ ሲሠራ መቆየቱን ያስታወሱት ዳይሬክተሩ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ የግድቡን ስኬት ለማፋጠን በተለያዩ መንገዶች እገዛ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የ5ኛ ዓመት የውሃ ሀብትና መስኖ ምኅንድስና ተማሪና የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሰቲ ተማሪዎች ኅብረት ዋና ጸሐፊ ተማሪ በረከት ብዙአየሁ ተማሪዎች 6ኛው አገራዊ ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ የድርሻቸውን እንዲወጡ የሚያስችል ግንዛቤ መፈጠሩን ገልጿል፡፡ የውጭ ጣልቃ ገብነትን ለመመከት ውስጣዊ አንድነታችንን ማጠናከር ይጠበቅብናልም ብሏል፡፡

የ4ኛ ዓመት የውሃ አቅርቦትና አካባቢ ምኅንድስና ተማሪና የተማሪ ኅብረት ም/ፕሬዝደንት ተማሪ የትምወርቅ ክብሩ በበኩሏ በዩኒቨርሲቲው ሁሉም ካምፓሶች ስለምርጫና ምርጫ ነክ ጉዳዮች ሥልጠና መሰጠቱን ተናግራለች፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች አብዛኛውን ወጣት የያዙ በመሆናቸው ለየትኛውም አካል አጀንዳ በመጋለጥ ሰላማችንን እንዳናጣ መጠንቀቅ ይኖርብናልም ብላለች፡፡

የ3ኛ ዓመት የቱሪዝምና ሆቴል ማኔጅመንት ተማሪ ዮናስ ፍቅረአብ በበኩሉ እንደ ኢትዮጵያዊነቴ የህዳሴው ግድብ የእኔም መሆኑን ተረድቼ አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነኝ ብሏል፡፡ ተማሪ ዮናስ በ2012 ዓ/ም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ለተወሰነ ጊዜ ትምህርት መስተጓጎሉን አስታውሶ ሀገራዊ ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅና ዳግም በትምህርት ሂደቱ ላይ እንቅፋት የሚሆኑ ክስተቶች እንዳይፈጠሩ ተማሪዎች ከምንጊዜውም በላይ በያሉበት ለሰላም ድምጻቸውን ማሰማት እንዳለባቸው ተናግሯል፡፡

በፕሮግራሙ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፣ 6ኛውን ሀገራዊ ምርጫና በሀገራችን ላይ እየተደረጉ ያሉ የውጭ ሀገራት ጫናዎችን በተመለከቱ አጀንዳዎች ዙሪያ ውይይት ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም ‹‹ግድቡ የእኔ ነው፣ አሜሪካና አውሮፓ ኅብረት ከኢትዮጵያ ላይ እጃችሁን አንሱ›› የሚሉና ሌሎችም መልዕክቶች ተደምጠዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት