‹‹የኢንጂነሪንግና ቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ለዘላቂ ልማት እና ተግዳሮቶች›› በሚል ርዕስ 2ኛው ዙር ሀገር አቀፍ ዓውደ ጥናት /2nd National Conference on Innovation and Challenges in Engineering and Technology for Sustainable Development›› ከሰኔ 9 - 10/2013 ዓ/ም በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ተካሂዷል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደገለጹት የዓውደ ጥናቱ ዓላማ በኢንጂነሪንግና በቴክኖሎጂው ዘርፍ በተካሄዱ የምርምር ሥራዎች የተገኙ ግኝቶችና የፈጠራ ሃሳቦች ላይ በጋራ በመወያየት ለቴክኖሎጂ ዕድገት ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲው በቴክኖሎጂና በኢንጂነሪንግ ዘርፍ ከፍተኛ ባለሙያዎችን በማፍራት በተጠቀሱት መስኮች ምርምር የመሥራት አቅሙን እያሳደገ መሆኑን ጉባዔው ማሳያ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ በዘርፉ ዕውቀትን ማመንጨት፣ ክሂሎትን ማዳበርና በምርምር አማካኝነት ቴክኖሎጂን ማሸጋገር ለኢንደስትሪ እድገትና ለዘላቂ ልማት ወሳኝ መሆኑን ፕሬዝደንቱ ጠቁመው ዩኒቨርሲቲው እንደ ምርምር ተቋምነቱ መሰል ተግባራት በማከናወን ለሀገሪቱ እድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበርከት ቁርጠኛ ነው ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአርክቴክቸር፣ የከተማ ፕላንና ህንፃ ኮንስትራክሽን ኢንስቲትዩት ተ/ፕ ፋሲል ጊዮርጊስ ባቀረቡት ቁልፍ ንግግር በከተማ ፕላንና ህንፃ ዲዛይን ገጠር ውስጥ ሊሠሩ የሚችሉ ከተሞችን በአካባቢያችን ያሉ ግብዓቶችን በመጠቀም እንዲሁም ዘመናዊውንና አገር በቀሉን በማዋሃድ የተሻለ የህንፃ ግንባታ ማካሄድ እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡ ይህም ለአካባቢው ማኅበረሰብ የተሻለ የኑሮ ደረጃን እንዲሁም የቴክኖሎጂ አቅርቦትንና አገልግሎትን ይፈጥራል ብለዋል፡፡ የተሻለ የፈጠራ ችሎታንና የቴክኖሎጂ ምርምርን ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግ ብሎም የኢንደስትሪ ትስስርን የበለጠ ማጠናከር እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡

ሳይንስ ከሀገር በቀል ዕውቀትና ጥበብ ጋር እንዲዋሃድ ስናደርግ ግንዛቤን በቀላሉ ወደ ማኅበረሰቡ የማስረጽና ወደ ተግባር የመለወጥ ዕድሉ ሰፊ ይሆናል ያሉት የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማ/አገ/ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ በቴክኖሎጂው ዘርፍ ያሉ ተግዳሮቶች ልንፈራቸው ሳይሆን የበለጠ መፍትሄ ለማበጀት በር ከፋች ሊሆኑ ይገባል ብለዋል፡፡ ችግርና ቴክኖሎጂ የማይነጣጠሉ እንደመሆናቸው መጠን ዛሬ የሚያጋጥሙንን የቴክኖሎጂ ተግዳሮቶች በጋራ በመሥራት ለእድገት እንጠቀመው ሲሉም አሳስበዋል፡፡ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች መጥተው የምርምር ሥራዎቻቸውን ያቀረቡትንና ለፕሮግራሙ መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱትንም አመስግነዋል፡፡

የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ተወካይ ዶ/ር ሙሉነህ ለማ በበኩላቸው በዓውደ ጥናቱ የቀረቡት የምርምር ሥራዎች በኤሌክትሮ ሜካኒካል፣ በኮምፒዩቲንግ፣ በህንፃ ግንባታ ጥራትና ውበት እንዲሁም በታዳሽ ኃይል የምርምር ማዕከል ሥር ያሉ የፀሐይ ኃይልን እና ነፋስን በመጠቀም ዙሪያ ትኩረት ያደረጉ መሆናቸውን ጠቅሰው ምርምሮቹ ችግሮችን የሚፈቱና እርስ በእርስ የምንማማርባቸው ናቸው ብለዋል፡፡

ዶ/ር ሙሉነህ አክለውም እያንዳንዱ የምርምር ግኝት ችግሮችን ለመፍታት ተጨባጭ በሆነ መንገድ ሥራ ላይ የሚውልበትን ሁኔታ ማመቻቸት ተገቢ እንደሆነና ከዚህም ጋር በተያያዘ በሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ከህንፃ ንድፍ አወጣጥ ጀምሮ ከመንገድና ኃይል አጠቃቀም ጋር የተያያዙ ምርምሮች ሲወጡ እንደ ዩኒቨርሲቲ የራሳቸውን ተጽዕኖ መፍጠር እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

በዓውደ ጥናቱ 17 ጥናታዊ ጽሑፎችና 4 የፖስተር ገለጻዎች በአርባ ምንጭ፣ አዲስ አበባ፣ ኮተቤ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ሀዋሳ፣ መቐለ፣ ሰመራ፣ ደብረ ብርሃን፣ መዳ ወላቡ፣ አሶሳ፣ ዲላ፣ አምቦና ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲዎች ቀርበዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት