Print

የዩኒቨርሲቲው ስፖርት አካዳሚ ከፌዴራልና ከደቡብ ክልል ስፖርት ኮሚሽኖች ጋር በመተባበር ከጋሞ ዞን ወረዳዎችና አርባ ምንጭ ከተማ ለተወጣጡ የስፖርት ባለሙያዎችና የስፖርት መምህራን ከሰኔ 2-11/2013 ዓ/ም የጤናና አካል ብቃት እንቅስቃሴ የአሠልጣኞች ሥልጠና ሰጥቷል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

ሥልጠናው በዋናነት በአካል ብቃት እንቅስቃሴ ምንነትና አሠለጣጠን ዘዴዎች፣ በስፖርት ሥነ-ምግብና በስፖርት የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና እርዳታ አሠጣጥ ላይ አተኩሮ በክፍል ውስጥ በጽንሰ ሃሳብና በተግባር ተደግፎ የተሰጠ መሆኑን በዩኒቨርሲቲው ስፖርት አካዳሚ ዳይሬክተር ዶ/ር ቾምቤ አናጋው ተናግረዋል፡፡ በሀገራችን ብሎም በአርባ ምንጭና አካባቢው ከጊዜ ወደ ጊዜ በኅብረተሰቡ ዘንድ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የማድረግ ልማድ እያደገ በመምጣቱ ሥልጠናውን ለመስጠት እንዳነሳሳ የተናገሩት ዶ/ር ቾምቤ ሥልጠናው በየአካባቢው የሚደረገው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የአሠለጣጠን ሂደት የስፖርት ሳይንስን የተከተለ እንዲሆን ለማድረግ የተዘጋጀ ነው ብለዋል፡፡

በሥልጠናው ከወረዳና ከተማ መዋቅሮች የሚሠሩ የስፖርት ባለሙያዎች፣ በአርባ ምንጭ ከተማ በግላቸው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚያሠሩ አሠልጣኞችና በከተማው በሚገኙ 4 ትልልቅ ሆቴሎች ውስጥ በዘርፉ የሚሠሩ ሠራተኞች የተሳተፉ መሆናቸውን የተናገሩት ዶ/ር ቾምቤ መሰል ሥልጠናዎችን በሌሎች በዩኒቨርሲቲው አቅራቢያ በሚገኙ አካባቢዎች ጭምር ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሥልጠናው ማጠቃለያ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የኢፌዲሪ ስፖርት ኮሚሽን ተወካይ አቶ ጌታቸው ተዋጀ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በማኅበረሰቡ ዘንድ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የማድረግ ልማድ እንዲዳብርና ጤናማ፣ ንቁና በአዕምሮውና በአካሉ የዳበረ ማኅበረሰብ ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ውስጥ የበኩሉን ሚና እየተወጣ በመሆኑ በኮሚሽኑ ስም ምስጋናቸውን አቅርበው፡፡ ኮሚሽኑ በቀጣይ ለስፖርቱ እንቅስቃሴ መስፋፋትና መጠናከር ከዩኒቨርሲቲውና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ተባብሮ ይሠራልም ብለዋል፡፡

የደቡብ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ም/ኮሚሽነር አቶ ብሩክ ቡናሮ በበኩላቸው የጋሞ ዞን ማኅበረሰቡን ያሳተፈ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በስፋት ከሚከናወንባቸው አካባቢዎች መካከል ዋነኛው መሆኑን ጠቅሰው ዩኒቨርሲቲው የሰጠው ሥልጠናም ስፖርቱ በተለያዩ አካባቢዎች በስፋት እንዲዳረስ የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሠልጣኞች ከሥልጠናው በኋላ ወደየአካባቢያቸው በመሄድ ያገኙትን ሳይንሳዊ ዕውቀትና ክሂሎት ተጠቅመው ማኅበረሰቡን በማሳተፍ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ሥልጠናዎችን መስጠት እንደሚገባቸውም ም/ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል፡፡

ከሥልጠናው ተሳታፊዎች መካከል ከምዕራብ ዓባያ ወረዳ የመጣው አቤኔዘር ጊዮርጊስ በሥልጠናው የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ማሰራት የሚያስችል በጽንሰ ሃሳብና በተግባር የተደገፈ ዕውቀትና ክሂሎት ማግኘቱን ተናግሮ በቀጣይ በአካባቢው በመሄድ ማኅበረሰበብ አቀፍ የአካል ብቃት እንቅሰቃሴን ለማስፋፋት እንደሚሠራ ተናግሯል፡፡

በኃይሌ ሪዞርት የአካል ብቃት እቅስቃሴ መ/ርት ህይወት መንግሰቱና በዩኒቨርሲቲው ስፖርት ሳይንስ ት/ት ክፍል መ/ርት የሆኑት ኤልሳቤጥ መስፍን በበኩላቸው ምንም እንኳን በዘርፉ እየሠራን ያለን ሙያተኞች ብንሆንም ሥልጠናው በርካታ አዳዲስ የጽንሰ ሃሳብና የተግባር ልምዶችን ያገኘንበት ነው ብለዋል፡፡ በቀጣይም ሥልጠና የመስጠት ፈቃድና የምስክር ወረቀት ያገኘን በመሆናችን በተለይ ሴቶችን ባሳተፈ መልኩ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ስፖርትን ለማስፋፋት እንሠራለን ብለዋል፡፡

በሥልጠናው የማጠቃለያ መርሃ ግብር ላይ ሥልጠናው በስኬት እንዲጠናቀቀ የበኩላቸውን ለተወጡ አካለትና አሠልጣኞች ምስጋና የቀረበ ሲሆን ለሠልጣኞች የምስክር ወረቀት በዕለቱ የክብር እንግዶች ተሰጥቶ የዕለቱ መርሃ ግብር ተፈጽሟል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት