ዩኒቨርሲቲው ለሕክምና አገልግሎት የሚውሉ የተለያዩ ቁሳቁሶችን ሰኔ 21/2013 ዓ.ም ለድል ፋና የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ድጋፍ አድርጓል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ድል ፋና የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል በከተማው በሆስፒታል ደረጃ አገልግሎት መስጠት በመጀመሩ መደሰታቸውን ገልጸው ከሕዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ የሚስተዋለውን የሕክምና አገልግሎት ጫና የሚቀንስ መሆኑን ተናግረዋል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፉ በጅምር ላይ ያለውን የሆስፒታሉን የአገልግሎት አቅም ከፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡ ቁሳቁሶቹ ተመላላሽና ተኝቶ ታካሚዎች የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚረዱ መሆኑን የተናገሩት ም/ፕሬዝደንቱ ሌሎች የሆስፒታሉን ክፍተቶች በጋራ እየሞላን አገልግሎቱ እንዲስፋፋ የበኩላችንን እንወጣለን ብለዋል፡

በዩኒቨርሲቲው የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ታምሩ ሽብሩ እንደገለጹት 8 ዓይነት ለተለያዩ ምርመራዎችና ለሕክምና አገልግሎት የሚውሉ ቁሳቁሶች በ428 ሺህ ብር በኮሌጁ በኩል ተገዝተው ቀርበዋል፡፡ የሕፃናት ተኝቶ መታከሚያ አልጋ፣ የጨቅላ ሕፃናት ማሞቂያ፣ የደም ግፊትና የልብ ትርታ መለኪያዎች፣ የልብ መመርመሪያ (ECG) መሣሪያ፣ የዐይንና ጆሮ መመርመሪያ መሣሪያዎችና የኦክስጂን መመርመሪያ ከተገዙት ቁሳቁሶች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

በአርባ ምንጭ ከተማ የድል ፋና የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል አስተዳደር አቶ ስንሻው አበበ ሆስፒታሉ በአሁኑ ሰዓት የተኝቶ ሕክምና አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ገልጸው በቅርቡ የቀዶ ጥገና ሕክምና የሚጀምር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በገባው ቃል መሠረት ላደረገው የሕክምና ቁሳቁሶች ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበው ድጋፉ የሆስፒሉን የሕክምና አገልግሎት በእጅጉ የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡

በቁሳቁስ ርክክብ ፕሮግራሙ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ የዩኒቨርሲቲው የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ አመራሮች እንዲሁም የድል ፋና ሆስፒታል አስተዳደርና የሕክምና ባለሙዎች ተገኝተዋል፡፡