Print

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሥራ ፈጠራ ልማት ማፍለቂያ ማዕከል ከአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ዘርፍ ጽ /ቤት ጋር በመተባበር ለአርባ ምንጭ ከተማ ስራ አጥ ወጣቶች በመሠረታዊ ሥራ ፈጠራ ክሂሎት ላይ የሥራ ፈጠራ ማነቃቂያ ሥልጠና ሰኔ 11/2013 ዓ.ም ሰጥቷል፡፡ ሥልጠናው ውስጣዊ ተነሳሽነት እንዲፈጠር የማነቃቂያ ሃሳቦች፣ መሠረታዊ የሥራ ፈጠራ ክሂሎት፣ የቢዝነስ ዕቅድ አዘገጃጀት እና መልካም አጋጣሚዎችን ወደ ሥራ ፈጠራ ሃሳብ መቀየር በሚያስችሉ ነጥቦች ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የማዕከሉ ዳይሬክተር ዶ/ር ወንድወሰን ጀረኔ አብዛኛው ሠልጣኞች ከቴክኒክና ሙያ ኮሌጅና ከዩኒቨርሲቲዎች የተመረቁ መሆናቸውን ጠቅሰው ሥልጠናው ባላቸው ዕውቀት ላይ የሥራ ፈጠራ አመለካከትን በማስረጽና ክሂሎታቸውን በማዳበር የሥራ ፈጣሪነት መንፈስን እንዲላበሱ ያደርጋል ብለዋል፡፡ ከዚህ ቀደም የራሳቸውን ሥራ በመፍጠር እየተንቀሳቀሱ ለሚገኙ የከተማዋ ወጣቶች ማዕከላቸው መሰል ሥልጠና መስጠቱን ያስታወሱት ዳይሬክተሩ ከየተቋማቱ ተመርቀው ሥራ ላልጀመሩና ያለሥራ ለቆዩ ሲሰጥ የመጀመሪያው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የማኔጅመንት ት/ክፍል መምህርና የሥልጠናው አስተባባሪ አቶ አበበ ዘየደ በበኩላቸው ሠልጣኞች የሥራ ፈጠራ ክሂሎት እንዲያገኙ በማስገንዘብ ሥራ መፍጠር እንዲችሉ ተነሳሽነትና መነቃቃት ለመፍጠር ያለመ ሥልጠና መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ወጣቶች ከሥልጠናው በኋላ በአካባቢያቸው በሚፈልጉት የሥራ መስክ ሲሰማሩ የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶችና የመፍትሄ እርምጃዎች እንዲረዱና እሳቤያቸውን እንዲያጎለብቱ አስተዋጽኦ ያደርጋልም ብለዋል፡፡

ሥልጠናውን የማኔጅመንት ት/ክፍል መምህራን የሰጡ ሲሆን በከተማው ወጣቶች፣ ሴቶችና ሕፃናት ጽ/ቤት የተመለመሉ 200 ሥራ አጥ ወጣቶች ተከታትለዋል፡፡ ወጣቶቹ በሥልጠናው መጨረሻ የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት