Print

ዩኒቨርሲቲው የ2013 ዓ/ም አዲስ ገቢ ተማሪዎችን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንትና ሌሎች የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች በተገኙበት ከሰኔ 28 እና 29/2013 ዓ/ም ተቀብሏል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

አዲስ ገቢ ተማሪዎች ያለምንም እንግልት ወደ ተመደቡበት ካምፓስ የሚሄዱበት መጓጓዣና አቅጣጫ የሚጠቁሙ የተማሪ ኅብረት ተወካዮች ቀድመው መዘጋጀታቸውን እንዲሁም በአገልግሎት ዘርፎች፣ ጸጥታን ከማስጠበቅ አንጻርና ኮቪድ-19ን ለመከላከል ዝግጅት መደረጉን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ገልጸዋል፡፡ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው በሚኖራቸው ቆይታ ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉ እና እርስ በእርስ በመዋደድ፣ በመከባበርና በመቻቻል የሀገር ሰላምን ለማስጠበቅ ዘብ እንዲቆሙ ዶ/ር ዳምጠው ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በ2013 የትምህርት ዘመን 4,300 ተማሪዎችን መቀበሉን ጠቁመው ለመማር ማስተማር ዝግጁ ለመሆንና ተማሪዎቹ ለዩኒቨርሲቲው አዲስ በመሆናቸው ምንም ዓይነት ችግር እንዳይገጥማቸው በዶርሚተሪ፣ በቤተ-መጽሐፍትና በመምህራን በኩል ቅደመ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን በሁሉም ካምፓሶች በመዘዋወር ምልከታ በማድረግ ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል፡፡ የተለያዩ መጽሐፍት በኦንላይንና በሃርድ ኮፒ በማሳተም ትምህርታቸውን የተሳለጠ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ከሀገር ሽማግሌዎች መካከል አቶ ሰዲቃ ስሜ ለተማሪዎቹ ባስተላለፉት መልዕክት ከተማዋ የሰላም፣ የፍቅር፣ የመተሳሰብና የመቻቻል ተምሳሌት በመሆንዋ በዩኒቨርሲቲው በሚኖራቸው ቆይታ ይህንን ማስቀጠልና ችግሮች ቢኖሩም በሰላማዊ መንገድ ከዩኒቨርሲቲው አመራሮችና አማካሪ አካላት መፍትሄ ማግኘት ትችላላችሁ ብለዋል፡፡

አዲስ ገቢ ተማሪዎች በሰጡት አስተያየት በኮቪድ-19 ምክንያት ከትምህርት ርቀው የቆዩ በመሆኑ ወደ ትምህርት ገበታ መመለሳቸው እንዲሁም የተደረገላቸው አቀባበል እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል፡፡ ከተለያዩ የግጭት መንስኤዎች ራሳቸውን በመጠበቅ በትምህርታቸው ውጤታማ መሆን እንደሚጠበቅባቸውም ተናግረዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት