Print

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ግብርና ሳይንስ ኮሌጅ ዓመታዊውን የምርምር ሥራዎች የመስክ ጉብኝት የኮሌጁ መምህራን፣ ተመራማሪዎችና ተማሪዎች በተገኙበት ሰኔ 24/2013 ዓ.ም አካሂዷል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

ጉብኝቱ በሰብል ልማት፣ በሆርቲካልቸር፣ በእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት፣ በተፈጥሮ ሀብት አያያዝና ደን ልማት እንዲሁም በግብርና ኤክስቴንሽንና በግብርና እሴት ሰንሰለት ላይ ተሠርተው ወደ መሬት የወረዱ ምርምሮች ውጤታማነትን ለመገምገም የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል፡፡ 

የኮሌጁ ዲን ዶ/ር ብርሃኑ ለማ ጉብኝቱ በዋናነት በአጭር ጊዜ ውስጥ መድረስ የሚችሉ፣ የተዘነጉና ትኩረት ያልተሰጣቸው የዕፅዋትና የሰብል ዓይነቶች በምርምር በማጥናት ለሙከራ ወደ መሬት በማውረድ ምን ደረጃ ላይ እንዳሉ ለመገምገምና ለአዳዲስ ተመራማሪዎች የዕውቀት ሽግግር ለማድረግ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኮሌጁ የምርምር ሥራዎች አስተባባሪ መምህር አግደው አበበ ከ85 በመቶ በላይ የሚሆነው የሀገራችን ሕዝብ በገጠር የሚኖርና ኑሮውን በግብርና የሚመራ በመሆኑ ተመራማሪዎች ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ምርምሮችን በማድረግ ወደ መሬት ማውረዳቸው የአርሶ አደሩን ተለምዷዊ አሠራር ከማሻሻል ባለፈ የማኅበረሰቡን ችግር ለመፍታት ያግዛል ብለዋል፡፡ በዓመቱ የተሠሩትን ሥራዎች በመመልከት የልምድ ልውውጥ ለማድረግና ውጤት ያመጡትን የምርምር ሥራዎችና የታዩ አመርቂ ተግባራትን ለቀጣይ ዓመት እንደ ግብዓት በመጠቀም ለማስቀጠል እንዲቻል ጉብኝቱ መዘጋጀቱንም ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በኮንሶ አካባቢ ለምግብነት ሲጠቀሙበት የነበረውና በአሁኑ ወቅት ኅብረተሰቡ እየተዋቸው ከሚገኙ የተክል ዓይነቶች መካከል በተለምዶ ‹‹ፓቅፓቃ›› ተብሎ የሚጠራው፣ በጋሞ ዞን ውስጥ ከሚበቅሉ በተልምዶ ‹‹ቀጾ››፣ ‹‹ሙልካኤ››ና ትንንሾቹ የቲማቲም ዝርያዎች እና የእንሰት ዝርያዎች በጉብኝቱ ምልከታ ተደርጓል፡፡ አትክልቶቹ በቆላማ አካባቢዎች የሚበቅሉ፣ ድርቅና በሽታን መቋቋም የሚችሉ፣ ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ፣ ብዙ ማዳበሪያና ኬሚካል የማይፈልጉ፣ ብዙ ጥንቃቄን የማይፈልጉ እንዲሁም በአጭር ጊዜ ውስጥ መድረስ የሚችሉ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም በጋሞ ዞን ከሚገኙ ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ የበግ ዝርያዎችን ሣር፣ ሽፈራው/ሀለኮና የምግብ ትራፊዎችን በመመገብ በቆይታቸው የተሻለ የክብደት ለውጥ ያመጡና ለእርባታ የሚሆኑ በጎች፣ በሐይቅ ላይ ብቻ ጥገኛ ከመሆን ማኅበረሰቡ በአካባቢው ትንንሽ የዓሳ ገንዳዎችን በመፍጠር የዓሳ ምርትን ማሳደግ እንዲያስችል ለሙከራ የተዘጋጁ ገንዳዎች እንዲሁም አረም ከመብቀሉ በፊትና በኋላ በተለይ በጥጥና በስንዴ ማሳዎች ላይ የሚታዩ አረሞችን ለማስወገድ ምርምር የተደረገባቸው 4 ዓይነት ጸረ-አረሞች ተጎብኝተዋል፡፡

በኮሌጁ በ2013 ዓ.ም በመጀመሪያ ዙር 11 እና በ2ኛ ዙር 30 በአጠቃላይ 41 የተጠናቀቁ ምርምሮች ጸድቀው ወደ ሥራ መግባታቸው ተጠቁሟል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት