የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ትምህርት ቤት ማኅበረሰብ አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ለአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ማኅበራዊ ፍርድ ቤት ዳኞች በተለያዩ የሕግ ጉዳዮች ላይ ከሰኔ 26-27/2013 ዓ/ም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ የማስረጃ ሕግ፣ የቤተሰብ ሕግ፣ የንብረት ሕግና የውርስ ሕግ በሥልጠናው ተዳሰዋል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በሕግ ትምህርት ቤት የሕግ ት/ክፍል ኃላፊና መምህር አቶ ጋድሴንድ ጎኖፋ እንደገለጹት የማኅበራዊ ፍርድ ቤት ዳኞች የኢትዮጵያ ማስረጃ ሕግን በተመለከተ ማስረጃ እንዴት መመዘን እንዳለበት በዝርዝር እንዲረዱና ውሳኔያቸው በማስረጃ የተደገፈ እንዲሆን የዕውቀት ክፍተቶችን ለመሙላት ሥልጠናው ተሰጥቷል፡፡

የሕግ ትምህርት ቤት መምህር የሆኑት መ/ር እንየው ደረሰ በበኩላቸው በማኅበራዊ ፍርድ ቤት ዳኞች ላይ የሚስተዋለውን የሕግ ክፍተት ለመሙላት ሥልጠናውን በተለያዩ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ እየሰጠን ነው ብለዋል፡፡ እንደ መምህር እንየው ገለጻ ለማንኛውም ዓይነት የቀበሌ አቤቱታ ማኅበራዊ ፍርድ ቤትን ከፍርድ ቤት በተሻለ በቅርቡ ማግኘት ስለሚቻል ማኅበረሰቡን ተደራሽ የሚያደርግ ነው፡፡ በሥልጠናው በተለይ የቤተሰብ ሕግ፣ ጋብቻ እና ከጋብቻ ጋር ተያይዞ ሊነሱ የሚችሉ ጉዳዮች ላይ መሠረታዊ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡

ሠልጣኞች በሰጡት አስተያየት ከሥልጠናው በርካታ ትምህርትና ግብዓት ማግኘታቸውን ገልጸው ከዚህ ቀደም በልምድ የሚሠሩ አሠራሮችን የሚያስቀርና ወደ ማኅበረሰቡ ይበልጥ ቀርቦ ለመሥራት የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት