የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የማኅበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ የዩኒቨርሲቲ ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ከጂኦግራፊና አካባቢ ጥናት ትምህርት ክፍል ጋር በመተባበር ከጋሞ ዞን ዕቅድና ፕላን መምሪያ፣ አየር ንብረትና አስተዳደር ጽ/ቤት፣ ቴክኒክና ሙያ መምሪያ፣ ኢንተርፕራይዝ መምሪያ፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ መምሪያ፣ ከተማ ልማት፣ ኢንቨስትመንት ጽ/ቤት፣ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ፣ ጤና መምሪያ እና ጋሞ ዞን አስተዳደር ጽ/ቤት ለተወጣጡ ባለሙያዎች በ‹‹GIS››፣ ‹‹GPS›› እና ሪሞት ሴንሲንግ ሶፍትዌሮች ዙሪያ ከሰኔ 7-11/2013 ዓ.ም ሥልጠና ሰጥቷል::  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የማኅበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ የዩኒቨርሲቲ ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኃይለማርያም አጥናፉ ዩኒቨርሲቲው ከዞኑ ጋር ባደረገው የመግባቢያ ስምምነት መሠረት አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለሚመለከታቸው የዞኑ ባለሙያዎች ተደራሽ ለማድረግ ሥልጠናው መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡ ሥልጠናው የተለያዩ መረጃዎችን የሚይዙበትና የኦንላይን መረጃ የሚያወርዱበትን ዘዴ ያካተተ በመሆኑ የመረጃ አያያዝና ሌሎችም ሥራዎቻቸው የዘመኑና የተቀላጠፉ እንዲሆኑ ይረዳቸዋል ብለዋል፡፡

የጂኦግራፊና አካባቢ ጥናት ት/ክፍል ኃላፊ አቶ አፈራ አዝመራው መሰል ሥልጠናዎችን ከዚህ ቀደም ሰጥተው እንደነበር አስታውሰው በቀጣይም ለተለያዩ የዞኑ መሥሪያ ቤቶች ለመስጠት አቅደን እየሠራን ነው ብለዋል፡፡ ሠልጣኞች መረጃዎችን የሚያገኙበትንና አቀናጅተው የሚሠሩበትን መሠረታዊ ዕውቀት ማግኘታቸውን አቶ አፈራ ተናግረዋል፡፡

አገሪቱ ባለችበት የእድገት ጎዳና ላይ አዳዲስ ሶፍትዌሮችን መሠልጠናችን መረጃን አደራጅቶ ለመያዝ ትልቅ ድርሻ አለው ያሉት ሠልጣኞች መሰል ሥልጠናዎች ተጠናክረው ቢቀጥሉ ማኅበረሰቡ ላይ የተሻለ ለውጥ ማየት ይቻላል ብለዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት