የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከውጪ ጉዳይ እና ከውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴሮች ጋር በመተባበር በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ወቅታዊ ሁኔታና የምሁራንን ትኩረት በሚሹ የሳይንስና የፐብልክ ዲፕሎማሲ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ የበይነ መረብ ውይይት ሰኔ 11/2013 ዓ/ም አካሂዷል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የኢፌዴሪ ም/ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያውያን ጊዜያቸውን፣ ገንዘባቸውንና ዕውቀታቸውን ያፈሰሱበት ታላቁ የህዳሴ ግድብ ፍሬው መታየት ሊጀምር በመሆኑ ከእውነት የራቁና ያልተገቡ መረጃዎችን በመልቀቅ ዲፕሎማሲያዊ ጫና ለማሳደር የሚሠሩ የውጭ ኃይሎችን በአንድነት ልንመክት ይገባል ብለዋል፡፡

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስትር ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ በበኩላቸው የከፍተኛ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማት ምሁራንና ሌሎች የዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ አካላት በዕውቀትና በሳይንስ ላይ የተመሠረቱ መረጃዎችን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተደራሽ በማድረግ የኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ድምጽ ተሰሚነት የመፍጠር ሚናቸውን አጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸው ገልጸዋል፡፡

የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚንስትር ዶ/ር ስለሺ በቀለ ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ ያሉ ወቅታዊ የግንባታ ሥራ ሂደቶችና እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች ላይ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን ባልተገባ ሁኔታ እየተሰራጩ ያሉ የሀሰት መረጃዎችን በዕውቅት ላይ ተመሥርቶ የማጥራት ሥራዎች ላይ ምሁራንና ሌሎች የዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ አካላት ሚናቸውን እንዲወጡና የሀገራችንን ችግሮች በጋራ መፍታት እንዲቻል አሳስበዋል፡፡

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ በፕሮግራሙ መቋጫ ላይ ባደረጉት ገለጻ በሀገራዊ ጥቅሞች ላይ የሚሰነዘሩ ማናቸውንም ጥቃቶች ለይቶ በዕውቀትና ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በማደራጀት ጥቃቶቹን በማክሸፍ ረገድ ምሁራን አና ተቋማት ሚናቸውን አጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደገለጹት እንደ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከ2003 ዓ/ም ጀምሮ አጠቃላይ ሠራተኛው የ3 ወር ደመወዙን እንዲሁም ተማሪዎች ከምግብ በጀታቸው ቀንሰው የህዳሴውን ግድብ ሲደግፉ ቆይተዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በውሃ መስክ ባለሙያዎችን ሲያበረክት መቆየቱን ጠቅሰው የህዳሴው ግድብ ከግብ እስኪደርስ የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን ብለዋል፡፡

የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር አብደላ ከማል በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ስለ ህዳሴው ግድብ ሰፋ ያሉ ዓውደ ጥናቶችን ማዘጋጀቱን እንዲሁም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎችንና ለሚዲያ የተለያዩ መረጃዎችን እየሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

የሃይድሮሊክ ፋከልቲ መምህር ዶ/ር ቦጋለ ገ/ማርያም እንደገለጹት የህዳሴውን ግድብ በተመለከተ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚገኙ ምሁራንና ተመራማሪዎች ተደራጅተው ሁሉም ሊሳተፉበት ይገባል፡፡ በተጨማሪም በማስተማር፣ በምርምርና መረጃዎችን ሰብስቦ በማደራጀት ትርጉም ያለው አቋም እንዲኖረን ዩኒቨርሲቲዎች የህዳሴውን ግድብ በተደራቢነት ብቻ ሳይሆን ትኩረት ተሰጥቶት ሊሠራ ይገባል ብለዋል፡፡

በፕሮግራሙ ላይ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማት ተማሪዎችና ምሁራን ሀገራዊ ጥቅሞችን ለማስከበር መረጃ የሚለዋወጡበት ‹‹የዓባይ ልጆች››/‹‹Nile Nations››/ የተሰኘ የፐብልክ ዲፕሎማሲ መተግበሪያ ሶፍትዌር በይፋ ተጀምሯል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ካውንስል አባላት፣ የዩኒቨርሲቲው አማካሪ ም/ቤት አባላት፣ ተጋባዥ መምህራን፣ የተማሪዎች ኅብረትና የሠላም ፎረም ተወካዮች በፕሮግራሙ ተሳትፈዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት