የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ በ‹‹Biodiversity Conservation and Management›› የትምህርት ፕሮግራም በ3ኛ ዲግሪ ለማስመረቅ የሚያስችለውን ቅድመ ሁኔታ አጠናቋል፡፡ ዕጩ ተመራቂ ዶ/ር ዘውድነህ ቶማስ ለምረቃ ብቁ የሚያደርገውን ጥናታዊ ጽሑፍ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው ምሁራን በተገኙበት ሰኔ 21/2013 ዓ/ም አቅርቧል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

ጥናታዊ ጽሑፉ ‹‹Ecology of small Mammals in Human-Modified Habitats Near the Western Shore of Lake Abaya, Southern Ethiopia›› በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ሲሆን ጥናታዊ ጽሑፉ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚስተዋሉት ከፍተኛ የመሬት አጠቃቀም ለውጦችና ለውጦቹን ተከትለው በሚፈጠሩ ችግሮች ላይ ያተኩራል፡፡ ከእነዚህም መካከል በተለይም የጀርባ አጥንት ያላቸው ተባዮች/Vertebrate Pests/ የተፈጥሮ ቤታቸው ሲፈርስ በወረራ መልክ ወደ ሰዎች መኖሪያ በመምጣትና ሰብል በማውደም ከፍተኛ ችግር የሚያስከትሉ በመሆኑ ችግሩን ከመቅረፍና ስነ-ምህዳሩን ከመጠበቅ አንጻር ባህላዊውን ዘዴ በቴክኖሎጂ በመደገፍ ዘላቂ የሆነ የተባይ መከላከያ ለአርሶ አደሩ ለማስተዋወቅ የምርምር ሥራው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያለው መሆኑ በጥናታዊ ጽሑፉ ተገልጿል፡፡

ዕጩ ተመራቂ ዶ/ር ዘውድነህ ቶማስ ለዚህ ቀን በመድረሱ ልዩ ስሜት እንደፈጠረበት ገልጾ በዩኒቨርሲቲው በነበረው ቆይታ ለደገፉት ሁሉ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡

በኮሌጁ በቅርቡ በተመሳሳይ ሁኔታ በሒሳብ ትምህርት መስክ አንድ ዕጩ ዶ/ር የመጨረሻ የምርምር ሥራውን አቅርቦ ለምረቃ እንደሚበቃ የተናገሩት የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ፈቃዱ ማሴቦ ዩኒቨርሲቲው ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በ3ኛ ዲግሪ ምሩቃንን ማፍራት መጀመሩ የዩኒቨርሲቲውን ዕድገት ጉዞና እመርታ የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት