የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የ2014 በጀት ዓመት ዓመታዊ ዕቅድ የዩኒቨርሲቲው ካውንስል አባላት በተገኙበት ሐምሌ 15/2013 ዓ/ም ተገምግሞ ጸድቋል፡፡ ከካውንስል አባላቱ በዕቅዱ ላይ ሊሻሻሉ፣ሊካተቱና ትኩረት ሊደረግባቸው የሚገቡ ነጥቦች ቀርበዋል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የስትራቴጂክ ዕ/ዝ/ት/ግ/ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አስፋው ደምሴ በዩኒቨርሲቲው የ10 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ መነሻነት ዕቅዱ የድህረ ምረቃና የቅድመ ምረቃ ትምህርት ተሳትፎ፣ የጥራት፣ የአግባብነት፣ የተደራሽነትና የፍትሃዊነት ጉዳዮች ትኩረት ተደርገው እንዲሁም የጥናትና ምርምር ሥራዎችም ከሀገር በቀል ዕውቀት ጋር ተቀናጅተው የማኅበረሰቡን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ስነ-ልቦናዊ ችግሮችን ለመፍታት እንዲያስችሉ ሆነው መታቀዱን ገልጸዋል፡፡

ዳይሬክተሩ አክለውም ዩኒቨርሲቲው ለደረጃው የሚመጥን የሰው ኃይል በማጠናከርና አቅምን በማጎልበት በዕቅዱ የተካተቱትን ዝርዝር ተግባራት በሁሉም ዘርፎች የሚዛናዊ ውጤት ተኮር ሥርዓትን መሠረት በማድረግ በተሳከ ሁኔታ ወደ መሬት ማውረድ ይገባል ብለዋል፡፡

በዕቅዱም ከቁልፍ አፈፃፀም ዕይታዎችች አንፃር፡- ጥራት፣ ተደራሽነት፣ አግባብነት፣ ፍትሃዊነትን ማረጋጥ፤ የተቋማዊ አቅምና ብቃት ማጎልበት፣ የትምህርት የማኅበረሰብ ተሳትፎ እና የሳይንስ ባህል ግንባታን ማጠናከር፤ የትምህርት ጥራት፣ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግርን ማጎልበት፣ የትምህርት መሠረተ ልማትና ፋሲሊቲ ማሳደግ፤ የዘርፈ ብዙ ተግባራት አፈጻጸም ማጠናከር የሚሉት በ2014 በጀት ዓመት የሚፈፀሙ ዓበይት የሚዛናዊ ውጤት ተኮር ተግባራቶች ሆነው ቀርበዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው የምርምር ዩኒቨርሲቲ እንደመሆኑ በየዘርፉ ዓመታዊ ዕቅዱ በተገቢው ሁኔታ እስከ ግለሰብ ፈፃሚ ድረስ ሚዛናዊ ውጤት ተኮር ሥርዓትን መሠረት አድርጎ በማውረድ በትጋት መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም በመማር ማስተማር ሂደት፣ በሀብት አጠቃቀምና የተቋሙን ገጽታ በመገንባት እንዲሁም መልካም አስተዳደርን በማስፈን ላይ በትኩረት ልንሠራ ይገባልም ብለዋል፡፡

የካውንስል አባላቱ በሰጡት አስተያየት ዕቅዱ በተገቢው ሁኔታ ተዘጋጅቶ መቅረቡን በማድነቅ በዕቅዱ ላይ ሊሻሻሉ፣ በተጨማሪነት ሊካተቱና ትኩረት ሊደረግባቸው የሚገቡ ነጥቦችን አንስተዋል፡፡ በተጨማሪም ዓመታዊውን የበጀት አቅም መሠረት በማድረግ የቤተ-ሙከራ፣ የምርምር ማዕካላትና የቤተ-መጽሐፍት ግብዓቶች እንዲሟሉ በትኩረት እንዲሠራ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት