የሳይንስና ክፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ‹‹ወደ ዕውቀት መር ኢኮኖሚ›› በሚል መሪ ቃል የመጀመሪያውን የትምህርት፣ የምርምር፣ የቴክኖሎጂና የኢንደስትሪ ትስስር ኮንቬንሽን ከሐምሌ 5-8/2013 ዓ/ም በአዲስ አበባ ኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል አካሂዷል፡፡ በኮንቬንሽኑ ላይ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተለያዩ የፈጠራና ቴክኖሎጂ ሥራዎችን፣ ወደ ማኅበረሰብ የወረዱ የምርምር ፕሮጀክቶችን እንዲሁም የኅትመት ውጤቶችን በማቅረብ ተሳትፎ አድርጓል፡፡   ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ምንስትር ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ ኮንቬንሽኑ የሳይንሳዊ ጥናትና ምርምር ውጤቶችን ለባለድርሻ አካላት ለማስተዋወቅና በከፍተኛ ትምህርት፣ በቴክኒክና ሙያ ተቋማትና በኢንደስትሪው ዘርፍ መካከል ለምርምርና ቴክኖሎጂ ልማት እንቅስቃሴ የሚያግዝ የእርስ በእርስ ትስስርና ቅንጅታዊ አሠራር እንዲጠናከር ለማድረግ ታልሞ የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመክፈቻ ፕሮግራሙ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢፌዴሪ ፕሬዝደንት ክብርት ወ/ሮ ሣህለወርቅ ዘውዴ መሰል የምርምርና የፈጠራ ዓውደ ርዕዮች መደረጋቸው ተሰጥኦ ያላቸውን የፈጠራና የምርምር ሰዎች ከማበረታታትና ከማስተዋወቅ እንዲሁም የምርምርና የፈጠራ ሥራዎች ተደራሽ እንዲሆኑ ከማድረግ አንጻር ጉልህ ፋይዳ ይኖራቸዋል ብለዋል፡፡ በጉብኝታቸው ወቅት ያዩዋቸው የፈጠራና የምርምር ሥራዎች አበረታች መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በበኩላቸው የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትንና ኢንደስትሪዎችን በአንድ ላይ በማሰባሰብ የምርምር፣ የቴክኖሎጂና የፈጠራ ሥራዎቻቸውን በዚህ መልክ የሚያቀርቡበትና እርስ በእርስ ልምድና ተሞክሯቸውን የሚለዋወጡበት መድረክ በማመቻቸቱ ሊመሰገን ይገባል ብለዋል፡፡ መድረኩ አንዱ ከሌላው ልምድ የሚወስድበትና በተቋማት መካከል ትስስርና የትብብር መንፈስ የሚፈጥር በመሆኑ ሀገራዊ ፋይዳው ጉልህ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በኮንቬንሽኑም እንደ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ባቀረብናቸው ሥራዎች በተለይም በእንሰት ፈጠራና ቴክኖሎጂዎች የማበረታቻ ሽልማትና ለቀጣይ ሥራችን አጋዥ ልምድና ተሞክሮዎችን ያገኘንበት ነበርም ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በኮንቬንሽኑ ላይ 12 የቴክኖሎጂና የፈጠራ ውጤቶችን፣ ወደ ማኅበረሰቡ የወረዱ የምርምር ፕሮጀክቶችንና የምርምር ኅትመት ውጤቶችን ይዞ መቅረቡን ተናግረዋል፡፡ በኮንቬንሽኑ በርካታ ልምዶችንና ተሞክሮዎችን ያገኘንበት ነበር ያሉት ዶ/ር ተክሉ በተለይ መድረኩ የዕውቀት መፍለቂያ የሆኑት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ኢንደስትሪዎችን ያገናኘ በመሆኑ ‹‹ወደ ዕውቅት መር ኢኮኖሚ›› የሚለው ዕቅድ እውን እንዲሆን ከማድረግ አንፃር የማይናቅ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ ኮንቬንሽኑ፣ ራሳችንን ያስተዋወቅንበት፣ ከሌሎች ልምድና ተሞክሮዎችን ያገኘንበት እንዲሁም ለቀጣይ ትስስሮች ግንኑነቶችን መፍጠር የቻልንበት ነበር ብለዋል፡፡ አክለውም እንደ ምርምር ዩኒቨርሲቲ በቀጣይ ደካማና ጠንካራ ጎኖቻችንን በመለየት የተሻሉ የምርምርና የፈጠራ ውጤቶችን ይዞ በመቅረብ ጠንካራና ተወዳዳሪ ለመሆን ካሁኑ በቅንጅትና በትብብር መሥራት ይጠበቅብናል ያሉት

ዶ/ር ቶሌራ ከዚህ አንፃር ዳይሬክቶሬታቸው የምርምር ዩኒቨርሲቲን የሚመጥኑ ተግባራትን ለማከናወን የእስከ ዛሬ ሥራዎችን በመገምገም ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ በማስቀመጥ እየሠራ ነው ብለዋል፡፡

በኮንቬንሽኑ ላይ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ባቀረባቸው የተለያዩ የፈጠራ፣ የቴክኖሎጂና የምርምር ፕሮጀክቶች ከጎብኚዎች አድናቆትን ያተረፈ ሲሆን ከጎብኚዎች መካከል ከሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የመጡት መ/ር ብዙነህ አድማሱ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ያቀረባቸው የፈጠራና የቴክኖሎጂ ውጤቶች አበረታች መሆናቸውንና የማኅበረሰቡን ችግር መቅረፍ የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል፡፡ በተለይ ዩኒቨርሲቲው ከእንሰት ተክል ጋር ተያይዞ ያቀረባቸው ቴክኖሎጂዎች እጅግ የሚደነቁ በመሆናቸው ይበልጥ የማስተዋወቅ ሥራ ተሠርቶባቸው ለገበያ የሚቀርቡበት ሁኔታ ላይ ሊሠራ ይገባል ብለዋል፡፡

ሌላኛው ጎብኚ የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ካሣሁን አሕመድ በበኩላቸው አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በሀገራችን ካሉ አንጋፋ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል የሚጠቀስ መሆኑን ጠቁመው ዩኒቨርሲቲው በኮንቬንሽኑ ላይ ይዞ የቀረባቸው ቴክኖሎጂዎች በተጨባጭ የሀገርንና የማኅበረሰብን ችግር የሚቀርፉ መሆናቸውን ታዝቤያለሁ ብለዋል፡፡ የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲም አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ካቀረባቸው የምርምርና የፈጠራ ቴክኖሎጂዎች በርካታ ልምዶችና ተሞክሮዎችን አግኝቷል ብለዋል፡፡

በኮንቬንሽኑ ማጠቃላያ መርሃ-ግብር ላይ የላቀ አፈፃፀም ላስመዘገቡ ፈጣሪዎች፣ ተማሪዎች፣ መምህራን፣ የሀገር በቀል ዕውቀት አበልፃጊዎች፣ ለተቋማት አመራሮችና ተቋማት ዕውቅናና ሽልማት ተበርክቷል፡፡ በዚህም መሠረት ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የእንሰት ተክል የምርትና የማብላላት ሂደትን ለማሻሻል የሚረዱ የፈጠራና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ይዘው የቀረቡት ዶ/ር አዲሱ ፈቃዱ በሀገር ደረጃ ከተወዳደሩ የፈጠራ ባለሙያዎች መካከል በላቀ የፈጠራ ውጤት 2ኛ በመውጣት የ 200 ሺህ ብር፣ የሜዳሊያ፣ የምሥክር ወረቀትና የክሪስታል አዋርድ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ በዚሁ ወድድር ዘርፍ የጂማ ዩኒቨርሲቲዎቹ ጀርሚያ ባይሳ እና ቦኤዝ ብርሃኑ 1ኛ ሲወጡ ከዚሁ ዩኒቨርሲቲ ደራርቱ ደረጀ እና ሽመልስ ንጉሴ እኩል ነጥብ በማምጣት 3ኛ ደረጃን በመያዝ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡

ዶ/ር አዲሱ ፈቃዱ በኮንቬንሽኑ ተሸላሚ በመሆናቸው በእጅጉ እንደተደሰቱ ተናግረው ለዚህ ስኬት ለመድረስ ከጎናቸው ለነበሩ አካላት ሁሉ ምሥጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ ኮንቬንሽኑ ከሽልማትና ከዕውቅና በላይ ከሌሎች ተቋማት ጋር ትስስር ከመፍጠር፣ አዳዲስ ልምዶችን ከማግኘትና ራስን ከማስተዋወቅ አንፃር ትልቅ አስተዋጽኦ አለውም ብለዋል፡፡ የተገኘው ዕውቅናና ሽልማት ብሎም የኤፌዴሪ ክብርት ፕሬዝደንትን ጨምሮ ከበርካታ ጎብኚዎች የተቸራቸው አድናቆት በቀጣይ ለሚሠሯቸው ሥራዎች በእጅጉ የሚያበረታታና የተሻሉ ሥራዎችን ሠርቶ ለማቅረብ የሞራል ስንቅ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

በዕለቱ ከየተቋማቱ ለተወጣጡ የላቀ አፈፃፀም ያስመዘገቡ 2 መምህራንና 2 ተማሪዎች ዕውቅናና ሽልማት የተበረከተ ሲሆን በዚህ መሠረት ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኢኮኖሚክስ ት/ክፍል ዶ/ር መስፍን ማንዛ እና ከውሃ አቅርቦትና አካባቢ ምኅንድስና ፋከልቲ መ/ርት ፌቨን ክንፈ የ25 ሺ ብር፣ የምሥክር ወረቀትና የሜዳሊያ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ ከተማሪዎች መካከል ከፋይናንስና ዴቭሎፕመንት ት/ክፍል ተማሪ አብዱልወኪል አባረሻድ እና ከፎሪስትሪ ት/ክፍል ተማሪ ሠራዊት ታደሰ የ10 ሺህ ብር፣ የምሥክር ወረቀትና የሜዳሊያ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡

በኮንቬንሽኑ የ4 ቀናት ቆይታ ‹‹የሰው ሀብት፣ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን የ10 ዓመት መሪ ዕቅድ እውን ማድረግ ተስፋዎችና ተግዳሮቶች››፣ ‹‹ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ለዘላቂ ልማት ከዓለም አቀፋዊ፣ አህጉራዊና አገራዊ ዕይታ አንፃር››፣ ‹‹የሳይንሳዊ ጆርናል ኅትመቶች ዕውቅና በኢትዮጵያ››፣ ‹‹የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት የሙያ ሥልጠና ለማጠናከር ከኢንደስትሪ ጋር የማስተሳሰር ሂደት ተስፋና ተግዳሮቶች›› በሚሉና ሌሎችም ርዕሶች ዙሪያ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው የተለያዩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ኃላፊዎችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት ሰፊ ውይይቶች ተደርገዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት