‹‹ኢትዮጵያን እናልብሳት›› በሚል መሪ ቃል በ3ኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ ቤሬ ተራራ ላይ በሚገኘው ተፋሰስና በሁሉም የዩኒቨርሲቲው ካምፓሶች ሐምሌ 20 እና 23/2013 ዓ/ም የችግኝ ተከላ ፕሮግራም አካሂዷል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደገለጹት ችግኝን የማልማት ሥራ በዩኒቨርሲቲው እንደ መደበኛ የማኅበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ እየተሠራ ሲሆን የሚተከሉትም ችግኞች በአካባቢው በቀላሉ ሊበቅሉ የሚችሉ መሆናቸው በጥናት የተረጋገጡ ናቸው፡፡ ከዚህም ባሻገር ከአካባቢው የአየር ሁኔታ አኳያ የመጣውን ለውጥም ዩኒቨርሲቲው በትኩረት ይከታተላል ብለዋል፡፡ ኅብረተሰቡ ችግኝ መትከልን እንደ ባህል ቢወስድና በየአካባቢው ቢተክል ወቅትን ተከትሎ ከሚከሰቱ የአየር ለውጥ ችግሮች መላቀቅ እንደሚቻል ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡፡

የመርሃ-ግብሩ ዋና ዓላማ በኢትዮጵያ ከአየር ለውጥ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት ችግኞችን በመትከል ኢትዮጵያን አረንጓዴ ማልበስ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ ተናግረዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች 8 የችግኝ ጣቢያዎች እንዳሉት የገለጹት ዶ/ር ተክሉ በ3ኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር እንደ ዩኒቨርሲቲ 30,000 ችግኞችን ለመትከል የታቀደ ሲሆን በቤሬ ተራራ ላይ 10,000 እንዲሁም በየካምፓሱ 6,494 ችግኞች መተከላቸውን ተናግረዋል፡፡ እስከ አሁን ባለው አፈፃፀም ከ750,000 በላይ ችግኞች በዞኑ የተሰራጩ ሲሆን በቀጣይም አንድ ሚሊየን ችግኞችን ለማሰራጨት አቅደናል ብለዋል፡፡ የተተከሉ ችግኞችን በልዩ ሁኔታ ለመንከባከብና ለመጠበቅ በዩኒቨርሲቲው የተቀጠሩ 30 ባለሙያዎች መኖራቸውን ዶ/ር ተክሉ ገልጸዋል፡፡

የመርሃ-ግብሩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት በተለይም አርባ ምንጭ ከተማ ሞቃታማ የአየር ጠባይ ያላት በመሆኑ ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን የተተከሉ ችግኖች እንዲፀድቁ ክትትል ማድረግ፣ ውሃ ማጠጣትና መንከባከብ ይኖርብናል ብለዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት