የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ማኅበረሰብ በቅርቡ በሞት ለተለዩት መ/ር ወርቁ ውበት የተሰማውን ሐዘን ለመግለጽ ሐምሌ 16/2013 ዓ.ም የሻማ ማብራት ፕሮግራም አካሂዷል፡፡ በፕሮግራሙ በአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት፣ በኮሌጁ ዲን፣ በመምህራንና በተማሪዎች በንግግር፣ በጽሑፍና በግጥም የሐዘን መግለጫ ቀርቧል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ በመምህር ወርቁ ድንገተኛ ኅልፈት የተሰማቸውን መደናገጥና ጥልቅ ሐዘን በራሳቸውና በዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ስም ገልጸው ለቤተሰብ፣ ለወዳጅ ዘመድና ለዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡ የመምህር ወርቁን ነፍስ እግዚአብሔር በሰላም ያሳርፋትም ብለዋል፡፡

መ/ር ወርቁ የዩኒቨርሲቲው ኬሚስትሪ ት/ ክፍል ምስጉን መምህርና ተመራማሪ ነበሩ ያሉት የኮሌጁ ዲን ዶ/ር ፈቃዱ ማሴቦ ከመማር ማስተማርና ምርምር ሥራ በተጨማሪ የሚሰጡ የአስተዳደር ሥራዎችንና ኃላፊነቶችን በትጋት የሚያከናውኑ ታታሪ መምህር እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡ መምህር ወርቁ ለራሳቸው፣ ለቤተሰባቸውና ለሀገር ብዙ መሥራት በሚችሉበት የወጣትነት ጊዜያቸው በድንገት በማለፋቸው ሐዘናቸውን መራር እንደሚያደርገው ዶ/ር ፈቃዱ ገልጸዋል፡፡

የኬሚስትሪ ት/ክፍል ኃላፊ መምህርት አትጠገብ አበራ መምህር ወርቁ በሥራቸው ብቃት ያላቸውና ታታሪ፣ ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር በመልካም ተግባቦት የሚኖሩና ሌሎችን መርዳት የሚወዱ በመሆኑ በት/ክፍሉ ለተሻለ ኃላፊነት መታጨታቸውን ገልጸው በድንገት ስለተለዩን ሐዘናችን ጥልቅ ነው ብለዋል፡፡

በመታሰቢያ ፕሮግራሙ የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት፣ የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ዲን፣ የኬሚስትሪ ት/ክፍል ኃላፊ፣ መምህራን፣ የአስተዳደር ሠራተኞችና ተማሪዎች ተገኝተዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት