Print

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ዳይሬክቶሬት የዳይሬክቶሬቱን የ2014 ዓ.ም ዕቅድ ሐምሌ 05/2014 ዓ.ም ገምግሟል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ


ዕቅዱ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አዋጅን ተከትሎ የተዘጋጀ መሆኑን የገለጹት የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ ዩኒቨርሲቲው እንደ ምርምር ዩኒቨርሲቲ በአዲስ መዋቅር ራሱን እያደራጀ እንደሚገኝና ከዚህ ቀደም የሚጠቀማቸውን የምርምር መመሪያዎች ከአዲሱ የአወቃቀር ሂደት ጋር በማገናዘብ ምርምሮችን የሚያካሂድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ውይይቱ በ2014 ዓ/ም በዩኒቨርሲቲው በሚሠሩ ምርምሮች ዙሪያ በዳይሬክቶሬቱ የተዘጋጀውን ዕቅድ ለማስተዋወቅና መሻሻል ያለባቸውን በማሻሻል፣ የጋራ ውሳኔ ላይ ለመድረስና ቀጣይ አቅጣጫን ለማስቀመጥ ያለመ መሆኑን የምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀ/ማርያም ጠቁመዋል፡፡ የሚሠሩ ምርምሮች በአብዛኛው በከተሞችና በጥቂት ቦታዎች ላይ ሳይወሰኑ ከከተማ ውጪ በሚገኙ ሌሎች አካባቢዎችም መድረስ እንዲችሉ ተደርገው መሠራት አለባቸው ብለዋል፡፡  
2014 ዓ/ም የሚሠሩ ሥራዎችን አጠናክሮ ለመቀጠል ከውስጥ ጀምሮ ዲፓርትመንት ከዲፓርትመንት፣ ኮሌጅ ከኮሌጅ፣ አንዱ ዩኒቨርሲቲ ከሌላው በሀገሪቱ ውስጥ ከሚገኙ እህት ዩኒቨርሲቲዎች፣ ከኢንደስትሪዎች፣ በዞንና በክልል ከሚገኙ የትምህርት፣ የደኅንነትና ሌሎች ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ጋር አብሮ መሥራት የሚያስችል የትብብር ማዕቀፍ በዕቅዱ ከተካተቱ ነጥቦች መካከል አንዱ ነው፡፡
የምርምር ውጤቶች ወደ ችግር ፈቺ ፕሮጀክቶች ተለውጠው ወደ ማኅበረሰቡ በመውረድ ችግሮችን እንዲፈቱ ማስቻል፣ በየኮሌጁ የሚካሄዱ የምርምር ሴሚናሮች፣ ዓለም አቀፍ የምርምር ኮንፍረንሶችና መሰል የምርምር ሥራዎችን የሚያጎሉ ፕሮግራሞችን ማጠናከር እንዲሁም ዩኒቨርሲቲው እንደ ምርምር ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ ፓርክ እንዲኖረው የሚሠሩ ተግባራት በዕቅዱ መያዝ እንዳለባቸው ከታዳሚዎች አስተያየት ተሰጥቷል፡፡
የኮሌጅ ዲኖች፣ የቴክኖሎጂና የውሃ ተክኖሎጂ ኢንስቲትዩቶች ዳይሬክተሮች፣ የታዳሽ ኃይል ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር፣ የሁሉም ኮሌጆች የምርምር ማዕከል ዳይሬክተሮችና አስተባባሪዎች እና የሳውላ ካምፓስ የምርምር ማዕከል አስተባባሪ በዕቅድ ውይይቱ ላይ ተገኝተዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት