Print

በ2013 ዓ.ም በዋናው ግቢ በቴክኖሎጂና ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩቶች ለተመደቡ 1,100 አዲስ ገቢ ተማሪዎች በቤተ-መጻሕፍት፣ በሬጅስትራርና በተማሪዎች አገልግሎት ዘርፍ አጠቃቀም እንዲሁም በተማሪዎች የዲሲፕሊን መመሪያ ዙሪያ ሐምሌ 16/2013 ዓ.ም ኦረንቴሽን ተሰጥቷል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉነህ ለማ እንደገለጹት ሥልጠናው አዲስ ገቢ ተማሪዎች በአገልግሎት አጠቃቀም ወቅት ችግር እንዳይገጥማቸውና ለትምህርታቸው እንቅፋት እንዳይሆን ከወዲሁ ጥንቃቄ ለመውሰድ የሚጠቅም ነው፡፡

የቤተ-መጻሕፍትና መረጃ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ረ/ፕ ሲሳይ ቱምሳ ስለ ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት ሲገልጹ ከዘርፈ ብዙ የቤተ-መጻሕፍት አገልግሎቶች አንዱ ሠርኩሌሽን ክፍል መሆኑን ተናግረው ተማሪዎች መታወቂያቸውን በማስያዝ ለ1 እና 2 ሣምንታት አልያም ለ1 ሰዓት የአጭር ጊዜ የመጻሕፍት ውሰት አገልግሎት ማግኘት ይችላሉ ብለዋል፡፡

የቴክኖሎጂና ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩቶች ማኔጂንግ ዳይሬክተሮችን ወክለው ገለጻ ያደረጉት አቶ ገዛኻኝ ዘርይሁን አስፈላጊውን ቅደም ተከተል ጠብቆ በተማሪዎች አገልግሎት በኩል ሁሉንም አገልግሎቶች ማግኘት እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡ በምግብ አገልግሎት በኩል ቅሬታ ቢኖር ቀጥታ ለምግብ ቤት ማቅረብና በቂ ምላሽ ካልተገኘ ለተማሪዎች ምግብ አገልግሎት አቅርቦ ምላሽ ማግኘት እንደሚቻልም ተናግረዋል፡፡

የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ተባባሪ ሬጂስትራር አቶ አክሊሉ ዓለማየሁ ተማሪዎች ባሉበት ሆነው በSMIS መመዝገብ መቻላቸው ሬጂስትራር አካባቢ የሚፈጠረውን ጫና እንደሚቀንስ ተናግረው ሥልጠናው ተማሪዎች ምዝገባ፣ የውጤት አሰጣጥና የመሳሰሉ ጉዳዮችን በአግባቡ እንዲያውቁ የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡

የተማሪዎች ዲሲፕሊን ባለሙያ የሆኑት አቶ የኋላእሸት ጉግሳ በበኩላቸው ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው በአንዳንድ አገልግሎት መስጫ ክፍሎች አካባቢ ሊገጥማቸው ከሚችለው የዲሲፕሊን ጥሰት ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ለማስቻል የተሰጠ ሥልጠና ነው ብለዋል፡፡

ከሠልጣኞች መካከል ተማሪ ብሩክ ካሳ ስለ ዩኒቨርሲቲው በአገልግሎት አሰጣጥ፣ በአካዳሚክና በዲሲፕሊን ጉዳዮች ዙሪያ ኦረንቴሽኑ ጥሩ ግንዛቤ መፍጠሩን ገልጿል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት