Print

በጫሞ ሐይቅ ዙሪያ ለሚሠራው አሳታፊ ዘላቂ የመሬትና የውሃ አያያዝ ሥራ ዕቅድ አዘገጃጀት ላይ ያተኮረ ሥልጠና ከ10 ወረዳዎች ለተወጣጡ 58 የልማት ጣቢያ ሠራተኞችና የዘርፉ ባለሙያዎች ከሐምሌ 13/2012 ዓ/ም ጀምሮ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ዓባያ ካምፓስ ለ7 ቀናት ተሰጥቷል፡፡ ሥልጠናው በጀርመን ልማት ተራድኦ ድርጅት/GIZ/ እና በግብርና ሚኒስቴር የዘላቂ መሬት አያያዝ ፕሮጀክት ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር ያዘጋጁት ነው፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ AMU-IUC ፕሮግራም ኃላፊና የውሃ ሥነ-ምኅዳር ተመራማሪው ዶ/ር ፋሲል እሸቱ እንደተናገሩት ሥልጠናው በቅርቡ የጫሞ ሐይቅ ተፋሰስ ላይ በጀርመን ልማት ባንክ ድጋፍና በግብርና ሚኒስቴር በዘላቂ የመሬት አያያዝ እና በኃይለማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን አስተባባሪነት 100 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ለሚሠራው የዘላቂ የመሬትና ውሃ ጥበቃ ሥራ የቅድመ ዝግጀት አካል ነው፡፡ ሥልጠናው ዘላቂ የመሬትና ውሃ አያያዝ ሥራ ዕቅድ ሳይንሳዊ መረጃዎችን ተከትሎ የሚዘጋጅባቸው መንገዶችና ዘዴዎች ላይ ለሠልጣኞች ግንዛቤ የሚፈጥር ነው፡፡ ሐይቆችን ከአደጋ በዘላቂነት ለመታደግ ሳይንሳዊ መረጃዎች ላይ ተመሥርቶ የሚሠራ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ በሐይቁ ተፋሰስ ላይ መሥራት የግድ ነው ያሉት ዶ/ር ፋሲል ሠልጣኞች ከሥልጠናው ያገኙትን ዕውቀትና ክሂሎት ተጠቅመው ማኅበረሰቡን በማስተባበር ሳይንሳዊ መረጃዎችንና አሠራሮችን ተከትለው እንዲሠሩ ሥልጠናው አጋዥ ነውም ብለዋል፡፡

በGIZ ኢትዮጵያ የተፋሰስ ልማትና የአሳታፊ ተፋሰስ ልማት ሥራ አስተባባሪ አቶ ግርማ ገ/ሐዋርያት አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በሐይቁ ዙሪያ ለረጅም ጊዜያት ምርምር ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረው በጥናቶቹ የተመለከቱ በሐይቁ ላይ የተጋረጡ አደጋዎችን ለመቅረፍ የተፋሰስ ሥራ መሥራት አስፈላጊ መሆኑ በመታመኑ የቅድመ ዝግጅት ሥራ አካል ሆኖ ከ10 ወረዳዎች ለተወጣጡ 58 የዘርፉ ባለሙያዎች ሥልጠና ተሰጥቷል ብለዋል፡፡ ሥልጠናው በአሳታፊ የተፋሰስ ልማት ሥራ ከዕቅድ አዘገጃጀት እስከ ውጤታማነት ምዘናና ግምገማ ድረስ ያሉ ሂደቶችን የሚያሳይና በተግባር ሥራዎች ጭምር ተደግፎ የተሰጠ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በደ/ብ/ብ/ሕ/ክ/መ እርሻና ተፈጥሮ ኃብት ቢሮ የዘላቂ መሬት አያያዝ ፕሮጀክት የተፋሰስ ልማት ባለሙያ አቶ አሰፋ ቸኮል በበኩላቸው የተፋሰስ ሥራ ከመጀመሩ በፊት የተፋሰስ ልማት ዕቅድ ሊዘጋጅ ስለሚገባ በቅርቡ የጫሞ ሐይቅ ተፋሰስ ላይ ለሚሠራው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ውጤታማነት ጉልህ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡ ከሥልጠናው በኋላ የሚሠሩ ሥራዎች ጫሞ ሐይቅ አደጋ ውስጥ ከመግባቱ በፊት ልንታደገው ስለምንችል ሠልጣኞችና ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለቀጣይ ሥራዎች ስኬት የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ከሥልጠናው ተሳታፊዎች መካከል ከአማሮ ወረዳ የመጣችው ወይንእሸት ወርቅነህ እና ከኮንሶ ዞን የመጡት አቶ አምሳሉ ስንታየሁ በሰጡት አስተያየት ከዚህ ቀደም የተፋሰስ ሥራዎችን ሲሠሩ ሐይቁን ታሳቢ አድርገው እንደማያውቁ ተናግረው አሁን ላይ በአካባቢያችን የምንሠራቸው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች ጠቀሜታቸው ዘርፈ ብዙ መሆኑን ተገንዝበናል ብለዋል፡፡ በሥልጠናውም በአሳታፊ የተፋሰስ ልማት ሥራ ጠቃሚ ሳይንሳዊ ዕውቀትና ክሂሎት ማግኘታቸውን ተናግረው ወደየአካባቢያቸው በመሄድ ሌሎችን በማሠልጠን የተግባር ሥራዎችን ለመሥራት ዝግጁ ነን ብለዋል፡፡

በጫሞ ሐይቅ ተፋሰስ ዘላቂ የመሬትና የውሃ አያያዝ ላይ የሚሠራ ከጀርመን ልማት ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ፣ በግብርና ሚኒስቴር በዘላቂ የመሬት አያያዝ እና በኃይለማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን አስተባባሪነት የሚመራ ለ5 ዓመታት የሚቆይ ፕሮጀክት የፊታችን መስከረም ወር ላይ ይፋ ሆኖ ሥራ እንደሚጀምር የተገለጸ ሲሆን ለፕሮጀክቱ መገኘት በሐይቁ ዙሪያ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን በተለይ በIUC ፕሮጀክት 6 የተደረጉ ሳይንሳዊ የምርምር ግኝቶችና የመፍትሔ አቅጣጫዎች ጉልህ ሚና እንደነበራቸው ታውቋል፡፡ ፕሮጀክቱ እንደ ሀገር ሐይቆችን መሠረት አድርጎ የሚሠራ፣ የመጀመሪያውና እንደ ፓይለት ተይዞ በሂደት ወደ ሌሎች ሥፍራዎች የሚሰፋ ሲሆን የፕሮጀክቱን የቅድመ ዝግጅት ሥራ ሥልጠና የተሳተፉት ሠልጣኞች ከጋሞ ዞን 6 ወረዳዎች፣ ከኮንሶ ዞን አንድ ወረዳ፣ ከቡርጂና አማሮ 3 ወረዳዎች የተወጣጡ ናቸው፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት