የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ 114 ሺህ ብር የሚያወጡ የሕክምና ቁሳቁሶችን ለሰላም በር የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሐምሌ 14/2013 ዓ/ም ድጋፍ አድርጓል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

ሰላም በር የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ዩኒቨርሲቲውን በደብዳቤ በጠየቀው መሠረት የደም ናሙና መመርመሪያና ሁለት የእናቶች ማዋለጃ አልጋ ድጋፍ መደረጉን የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር ወ/ሮ ወይንሸት ገብረፃዲቅ ገልጸዋል፡፡

የደም ናሙና መመርመሪያው 78 ሺህ ብር እና የማዋለጃ አልጋው 36 ሺህ ብር በድምሩ የሕክምና ቁሳቁሶቹ 114 ሺህ ብር ያወጣሉ ያሉት ዳይሬክተሯ እንደ ኮሌጅ በተለያዩ ቦታዎች ሙያዊና ቁሳዊ ድጋፎች እንደሚደረጉና አዳዲስና እያደጉ ያሉ ሆስፒታሎችን በቁሳቁስ የማደራጀት ሥራ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የሰላም በር የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ አቶ አስፋው አዴቶ የአካባቢው ኅብረተሰብ ከዚህ ቀደም ወደ ወላይታና አርባ ምንጭ ሆስፒታሎች በመሄድ አገልግሎቱን ያገኝ እንደነበር አስታውሰው አገልግሎቱን በአቅራቢያቸው ማግኘታቸው እንግልቱን ይቀንሳል ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ጥያቄያቸውን ተቀብሎ ላደረገው ድጋፍ የተሰማቸውን ደስታና ምስጋናም አቅርበዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት