የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሴኔት ነሐሴ 4/2013 ዓ/ም ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ለ 3 መምህራን የተባባሪ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ የሰጠ ሲሆን በሌሎች የተለያዩ ጉዳዩችም ላይ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በዕለቱ ከውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዶ/ር አብደላ ከማል እና ዶ/ር ሳሙኤል ዳጋሎ እንዲሁም ከሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዶ/ር አሲር ማኒላል (Dr Aseer Manilal) በዩኒቨርሲቲው ሴኔት መመሪያ ላይ የተቀመጡ 4 ዓመት ወይም 8 ሴምስቴር ያልተቋረጠ የመማር ማስተማር፣ የአመራርነትና የኮሚቴ እና የማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራዎች ተሳትፎ እንዲሁም የምርምር ኅትመት ጋር ተያይዘው የተቀመጡ መስፈርቶችን በማሟላታቸው ከረዳት ፕሮፌሰርነት ወደ ተባባሪ ፕሮፌሰርነት አካዳሚክ ደረጃ እንዲሸጋገሩ ተወስኗል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በዕለቱ በዩኒቨርሲቲው በተለያዩ ትምህርት መስኮች በ3ኛ ዲግሪ፣ በ2ኛና በመጀመሪያ ዲግሪ በመደበኛ፣ በርቀትና በክረምት መርሃ-ግብሮች ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ በመጀመሪያ ዲግሪ 206፣ በ2ኛ ዲግሪ 182 እንዲሁም በ3ኛ ዲግሪ 3 በአጠቃላይ 391 ተማሪዎች ለምረቃ የሚጠበቅባቸውን መስፈርት ማሟላታቸውን በማረጋገጥ ለምረቃ እንዲበቁ ሴኔቱ አጽድቋል፡፡

ሴኔቱ ከመማር ማስተማርና ሌሎች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ የሰጠ ሲሆን የ2013 ተማሪዎች የምረቃ በዓልም መስከረም 29/2014 ዓ/ም በአርባ ምንጭ እና መስከረም 30/2014 ዓ/ም በሳውላ ካምፓስ አንዲከበር ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት