Print

የዩኒቨርሲቲው መምህራን፣ ተመራማሪዎችና የአስተዳደር ሠራተኞች ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ድጋፍ ለማድረግ ነሐሴ 8/2013 ዓ/ም በዋናው ግቢ ባካሄዱት ውይይት የ 1 ወር ደመወዛቸው በበጀት ዓመቱ ተቆራጭ ተደርጎ ድጋፍ እንዲደረግ ወስነዋል፡፡ ከገንዘብ ድጋፉ በተጨማሪ ፈቃደኛ ተሳታፊዎች የደም ልገሳ አከናውነዋል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ 

የዩኒቨርሲቲው የአስተዳደር ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር መልካሙ ማዳ በአሁኑ ሰዓት ሀገራችን ከተጋረጠባት የውጭና የውስጥ ኃይሎች የተቀናጀ ሴራ ነፃ እንድትሆን እና ዳር ድንበሯ ተከብሮና ሰላሟ ተረጋግጦ ወደ ልማት ጎዳና እንድትገባ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ከመንግሥት ጎን በመሆን በገንዘብ፣ በዓይነት እንዲሁም እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ድረስ በመክፈል የራሱን ድርሻ መወጣት ይገባዋል ብለዋል፡፡ በቀጣይም በተማሪዎች በኩል የሚደረጉ የገንዘብና የደም ልገሳ መርሃ-ግብሮች እንዲሁም ከተቋሙ ማኅበረሰብ በአጠቃላይ በዓይነት በሚደረጉ ድጋፎች ላይ በትኩረት እንደሚሠራ ዶ/ር መልካሙ ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ በበኩላቸው የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ በተለያዩ ጉዳዮች ለሀገር ጥሪ ምላሽ ሲሰጥ የቆየ መሆኑን አስታውሰው በአሁኑ ሰዓትም ሀገርን ለማዳን በተላለፈው ጥሪ መሠረት እንደ ተቋም ሠራተኛም ሆነ እንደ ዜጋ በጦርነት ለተፈናቀሉ ወገኖችና ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ድጋፍ ምላሽ መስጠት ይገባል ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የባህልና ቋንቋ ጥናት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶ/ር ሰኢድ አሕመድ ባቀረቡት የውይይት መነሻ ሠነድ እንደገለጹት ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ በርካታ ፈተናዎች ቢገጥሟትም በድል የምትወጣ፣ ለውጭ ወራሪዎች የማትንበረከክና በወቅታዊ ፈታናዎች ሳትበገር ህልውናዋን ጠብቃ የቆየች ናት፡፡ ኢትዮጵያ የገጠማት ፈተና ወቅታዊ በመሆኑ ይህንን ለመሻገር የሚያስችል አስተዋጽኦ በግለሰብም ሆነ በተቋም ደረጃ በቅንጅት በማበርከት ትውልዱ አኩሪ ታሪክ ሠርቶ ለቀጣዩ ትውልድ ሀገርን በክብር ማስረከብ ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ሀገርን እንደ ሀገር ለማስቀጠል ኢትዮጵያዊያን በጋራ በመቆም በአካል በመሄድ፣ በገንዘብ፣ በዓይነትና በተለያዩ አማራጮች ድጋፍ በማድረግ ታሪካዊ ሀገር የማፍረስ ሴራውን ማክሸፍ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የሀገር አፍራሽ ቡድኖችን ተልዕኮ የሚደግፉ፣ ተገቢ ያልሆነ ፕሮፓጋንዳ የሚነዙና በማኅበራዊ ሚዲያ ገፆቻቸው የሚያጋሩ አካላት ተዓማኒነት ያለውን መረጃ ለይተው እንዲረዱና ከድርጊታቸው እንዲታቀቡም አሳስበዋል፡፡

በውይይቱ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ የካውንስል አባላት፣ መምህራን፣ ተመራማሪዎችና የአስተዳደር ሠራተኞች ተገኝተዋል፡፡ ከመምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች በ 1 ዓመት ጊዜ ውስጥ የሚከፈል የ 1 ወር ደመወዝ በድምሩ 27.6 ሚሊየን ብር ድጋፍ የተደረገ ሲሆን በዓይነት 13 ዩኒት ደም ተሰብስቧል፡፡ በቀጣይነትም በሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ አስተባባሪነት በሁሉም ካምፓሶች የደም ልገሳ መርሃ-ግብር እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት