Print

ዩኒቨርሲቲው ለ2013 ዓ.ም አዲስ ገቢ ተማሪዎች ሐምሌ 23/2013 ዓ.ም በዋናው ግቢ የእንኳን ደህና መጣችሁ ፕሮግራም አካሂዷል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ተማሪዎቹ ስለዩኒቨርሲቲው የተሰጣቸውን ኦሬንቴሽንና የሕይወት ክሂሎት ሥልጠና ተግባራዊ በማድረግ የዩኒቨርሲቲ ቆይታቸውን እንዲያሳኩ አሳስበዋል፡፡ ማንበብ ያለባችሁ ለፈተና ሳይሆን በቂ ዕውቀት ለመጨበጥ ይሁን ያሉት ፕሬዝደንቱ ተማሪዎቹ በቆይታቸው መምህራንን፣ ቤተ-መጻሕፍትን፣ ቤተ-ሙከራዎችንና ሌሎችንም አገልግሎቶች በአግባቡ እንዲጠቀሙ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ላለፉት በርካታ ዓመታት ጠንካራና የተሻለ ትምህርት በመስጠት የሚታወቅ መሆኑን ጠቅሰው ተማሪዎች ዋነኛ ተልዕኳቸው የሆነውን ትምህርት ለማሳካት በሚፈለገው መልኩ ለመማር ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ አሳስበዋል፡፡

የጋሞ አባቶችን ወክለው መልዕክት ያስተላለፉት አቶ ሰዲቃ ስሜ ለሰላም ዘብ በሚቆመው የጋሞና የአርባ ምንጭ ከተማ ሕዝብ ውስጥ ለመኖር እንኳን ደህና መጣችሁ፤ በቆይታችሁ ሁሉ እግዚአብሔር ይርዳችሁ ብለዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ኅብረት ፓርላማ ፕሬዝደንት ተወካይ ተማሪ አንሙት ጎዴ ተማሪዎች ለግቢው አዲስ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ እንዳይሸበሩ አቀባበል በማድረግ በመኝታ፣ በምግብ፣ በጤናና በሌሎችም አገልግሎቶች ኅብረቱ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ተናግሯል፡፡ ለወደፊቱም ከዩኒቨርሲቲው አመራሮች ጋር በመቀናጀት ምቹና ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደትን ለመፍጠር እንሠራለን ብሏል፡፡

ከአዲስ ገቢ ተማሪዎች መካከል ተማሪ ነፃነት ደረጀ በተደረገላቸው አቀባበል መደሰቷን ገልጻ የጋሞ አባቶች ምርቃትና የዩኒቨርሲቲው አመራሮች ያስተላለፉት መልዕክት በትምህርታችን እንድንነቃቃ ያደርገናል ብላለች፡፡

በፕሮግራሙ በ2013 ዓ/ም በዩኒቨርሲቲው ከተመደቡ ተማሪዎች ከየክፍሉ ሁለት ሁለት ተወካዮች፣ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የጋሞ አባቶች፣ የአርባ ምንጭ ከተማ ከንቲባ ተወካይ፣ የአርባ ምንጭ ከተማ ማዘጋጃቤታዊ አገልግሎት ኃላፊ የተማሪዎች ኅብረት ፕሬዝደንት ተወካይ፣ የሰላም ፎረም ፕሬዝደንት ተወካይና ሌሎችም የሚመለከታቸው አካላት የተገኙ ሲሆን በፕሮግራሙ ፍፃሜ የ3ኛው ዙር አረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ አከናውነዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት