ዶ/ር ዮሴፍ ብሩ ገ/ጊዮርጊስ በቀድሞው ጅማ ክ/ሀገር ጅማ ከተማ ሐምሌ 29/1961 ዓ.ም ተወለዱ፡፡ የ1ኛና 2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በጅማ ከተማ ተከታትለዋል፡፡

የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በ1984 ዓ/ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሲቪል ምኅንድስና፣ 2ኛ ዲግሪያቸውን መጋቢት 1990 ዓ/ም በግንባታ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ህንድ ሀገር ከሚገኘው ሩርኪ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም 3ኛ ዲግሪያቸውን ታኅሣሥ 21/1999 ዓ/ም ሕንድ ሀገር ከሚገኘው ‹‹Indian Institute of Technology›› በሲቪል ምኅንድስና ተቀብለዋል፡፡

ዶ/ር ዮሴፍ በ1985 ዓ/ም በአርባ ምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በረዳት ምሩቅ II አካዳሚክ ደረጃ በኮንትራት የተቀጠሩ ሲሆን መስከረም 1/1986 ዓ.ም ወደ ሌክቸረር አካዳሚክ ማዕረግ አድገዋል፡፡ ከጥቅምት 15/1987 ዓ/ም ጀምሮ የስትራክቸራል ምኅንድስና ት/ክፍል ኃላፊ፣ ከኅዳር 1/1991 - ሚያዝያ 30/1994 ዓ/ም የማታና ተከታታይ ትምህርት ክፍል አስተባባሪ፣ ከግንቦት 1/1994 - ታኅሣሥ 16/2001 ዓ/ም የአርባ ምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የአስተዳደር ልማት ም/ዲን፣ ከታኅሣሥ 17/2001 - የካቲት 17/2003 ዓ/ም የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክና ምርምር ም/ፕሬዝደንት፣ ከየካቲት 18/2003 - ሰኔ 4/2004 ዓ/ም የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ 3ኛው ፕሬዝደንት በመሆን አገልግለዋል፡፡

ዶ/ር ዮሴፍ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ለቀው ከወጡ በኋላ በተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሀገራቸውን በዕውቀታቸው ያገለገሉ ሲሆን በኮንስትራክሽንና ከተማ ልማት ሚኒስቴር በዳይሬክተርነት፣ በኢትዮጵያ ፕሮጀክት ማኔጅሜነት ኢንስቲትዩት በዋና ሥራ አስኪያጅነት፣ በአያት መኖሪያ

ቤቶች ድርጅት በዋና ሥራ አስኪያጅነት፣ በጊፍት የመኖሪያ ቤቶች ድርጅት በዋና ሥራ አስኪያጅነት፣ በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን፣ ዲዛይንና ሱፐርቪዥን ኮርፖሬሽን በቦርድ አባልነት፣ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢነትና አባልነት እንዲሁም በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ከመጀመሪያ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ለሚማሩ ተማሪዎች በተጋባዥ መምህርነትና በምርምር ሥራ አማካሪነት ሠርተዋል፡፡

ዶ/ር ዮሴፍ ባጋጠማቸው ድንገተኛ ሕመም ምክንያት ከሐምሌ 28/2013 ዓ.ም ጀምሮ በየካ ኮተቤ ሆስፒታል በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ነሐሴ 11/2013 ዓ.ም በተወለዱ በ52 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡

ዶ/ር ዮሴፍ ብሩ ባለትዳርና የሦስት ሴት ልጆች አባት የነበሩ ሲሆን የቀብር ሥነ-ሥርዓታቸው ሐሙስ ሐምሌ 13/2013 ዓ/ም አያት አደባባይን አልፎ ወደ መቄዶኒያ የአረጋዊያን መረጃ ማዕከል በሚወስደው መንገድ ከሚገኘው የመኖሪያ ቤታቸው በመነሳት በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ከቀኑ 9፡00 ሰዓት ቤተሰቦቻቸው፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸውና የሥራ ባልደረቦቻቸው በተገኙበት ይፈጸማል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በዶ/ር ዮሴፍ ብሩ ሞት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን እየገለጸ ለቤተሰቦቻቸው፣ ለሥራ ባልደረቦቻቸውና ለወዳጅ ዘመዶቻቸው መጽናናትን ይመኛል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት