የልማት ሙሉ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪዎችን የእንግሊዝኛ ቋንቋ የንባብ ክሂሎት ለማሻሻል በዩኒቨርሲቲው እንግሊዝኛ ቋንቋ መምህራን የሚሠራው ፕሮጀክት በተማሪዎች ዘንድ ለውጥ እያሳየ መሆኑ ተገልጿል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶ/ር መለሰ መንገሻ በፕሮጀክቱ የምርምር ውጤትን መነሻ በማድረግ ከ2ኛ- 4ኛ ክፍል በፈተና ከተለዩ ማንበብ የማይችሉ 50 ተማሪዎቸ መካከል ለ20 ፈቃደኛ ተማሪዎች የተለያዩ ድጋፎች እንዲሁም ለመምህራን ሥልጠናዎችን ሲሰጡ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡

እንደ ዶ/ር መለሰ ገለጻ ተማሪዎቹ አናባቢ ፊደላት የተለያዩ ድምጾች እንዳሏቸው ከተረዱ ሌሎችን ማንበብ በቀላሉ እንደሚችሉ የጥናታቸው ውጤት ስለሚጠቁም ለሥራው አጋዥ የሚሆኑ ካፒታልና ስሞል ፊደላትን፣ ከፊደላት የተመሠረቱ ቃላትን እና ከቃላቱ የሚዛመዱ ሥዕሎችን በአጠቃላይ 40 ባነሮችንና የተለያዩ መልመጃዎችን የያዙ ሞጁሎችን አሳትመዋል፡፡ በጥልቀት ለተማሪዎች በተሰጠው ድጋፍም በአማካይ ከቅድመ መደበኛ ጀምረው ከ4-6 ዓመት ተምረው ያላወቁትን በአንድ ወር ውስጥ ፊደላትን ከመለየት ባሻገር ቃላትን ማንበብ ችለዋል፡፡

የልማት ሙሉ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት ርዕሰ መምህር አቶ አዳነ ገዛኸኝ በተማሪዎቹ ዘንድ የታየው ለውጥ በፕሮጀክቱ በተሠራ ተከታታይና ቋሚ ድጋፍ መሆኑን ገልጸው በቀጣይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ቅንጅት በመፍጠር በቋንቋው ደከም ያሉ ተማሪዎችን በማስተማር የታየውን ለውጥ ለማስቀጠል በትጋት እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡

የት/ቤቱ የእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህርት ብርቱካን በላይነህ ከዚህ ቀደም ተማሪዎቹ ፊደላትን ከመዘመርና ከመጥራት ባለፈ ሌሎች ጉዳዮችን ባለመለየታቸው ለማንበብ ይቸገሩ እንደነበር አስታውሰው አሁን ግን ድምጹንና ከፊደላት የተመሠረቱ ቃላትን ለይተው በመማራቸው ከፍተኛ ለውጥ ማምጣታቸውንና ለመምህራንም ጥሩ የማስተማሪያ ስነ-ዘዴ ያሳወቃቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በፕሮጀክቱ ድጋፍ ያገኘችው የ3ኛ ክፍል ተማሪ እንያት ስምዖን ከዚህ በፊት የእንግሊዝኛ ቋንቋ ንባብ እንደማትችል ገልጻ ባገኘቻቸው የተለያዩ ድጋፎች የንባብ ክሂሎቷ ማዳበሯን ተናግራለች፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት