የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ AMU-IUC ፕሮግራም ከGHENT ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር አጥቢ እናቶች ከ6 ወር በታች የሆኑ ሕፃናትን የእናት ጡት ወተት ብቻ ማጥባታቸውን ለመለየት የሚያገለግል የምርምር መለኪያ ዘዴ ላይ ከሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የተለያዩ ትምህርት ክፍሎች ለተወጣጡ 40 መምህራን ነሐሴ 7/2013 ዓ/ም የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በኮሌጁ የኅብረተሰብ ጤና ት/ክፍል መምህር የሆኑት አቶ ዋንዛሁን ጎዳና እንደገለጹት ሥልጠናው እናቶች ከ0-6 ወር ድረስ ልጆቻቸውን የጡት ወተት ብቻ ማጥባት አለማጥባታቸውንና ሕፃናት ተጨማሪ ነገር መውሰድ አለመውሰዳቸውን ማረጋገጥ የሚያስችል ሳይንሳዊ ዘዴ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ይህንን ሳይንሳዊ ዘዴ ተግባራዊ ማድረጋቸውን ከዚህ በፊት እናቶችን በመጠየቅ በሚገኘው መረጃ መሠረት የሚዘጋጁ ሪፖርቶችን በማስቀረት በተሳሳተ መረጃ በተዘጋጁ ሪፖርቶች ምክንያት በሕፃናት ላይ የሚከሰቱ በሽታዎችን ከመከላከል አንጻር ጉልህ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡

የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሥነ-ምግብ መምህርና የAMU-IUC ፕሮገራም የፕሮጀክት 3 አስተባባሪ አቶ እሸቱ ዘርይሁን በበኩላቸው ሥልጠናው አንድ እናት ልጇን የእናት ጡት ወተት ምን ያህል እንዳጠባች ለመለካት የሚያስችል በቤተ-ሙከራ የሚሠራ አዲስ ዘዴ ላይ ያተኮረ መሆኑን ተናግረው በዘርፉ ምርመር ለሚሠሩና ለመሥራት ላሰቡ መምህራን ሥልጠናው በእጅጉ ጠቃሚ ነው ብለዋል፡፡

ሠልጣኝ ረ/ፕ መልካሙ መርዕድ በሰጡት አስተያየት ሥልጠናው እናቶች በመጀመሪያ 6 ወር ጊዜ ውስጥ ለሕፃናት ምንም ተጨማሪ ምግብ አለመስጠታቸውንና ሕፃናት የእናት ጡት ወተት ብቻ ማግኘታቸውን በቤተ-ሙከራ መለካት እንድንችል የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡ ከእናቶች ብቻ ከሚሰጡ መረጃዎች ይልቅ በትክክለኛው መረጃ ላይ ተመሥርቶ ሪፖርት ለማዘጋጀት ስለሚያስችል ዘዴው ችግር ፈቺ ምርምሮችን መሬት ላይ ወርዶ ለመሥራት አቅጣጫ ጠቋሚ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት