Print

የቆላማ አካባቢ በሽታዎች ሀገር አቀፍ ዓመታዊ የምክክር ጉባዔ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከነሐሴ 18-21/2013 ዓ/ም ተካሂዷል፡፡ በጉባዔው በወላይታ ዞን በሙከራ ላይ የሚገኘው የʻʻGeshiyaroʼʼ ፕሮጀክት አሁናዊ የመስክ ምልከታና የፕሮግራሙ የ2013 በጀት ዓመት የሥራ አፈፃፀም ግምገማ ተካሂዷል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ     

የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎቻችን ትኩረት የሚሹ የቆላማ አካባቢ በሽታዎችን በተመለከተ ምርምሮችን በሰፊው ሊሠሩ እንደሚገባ ገልጸው በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በዘርፉ የተጀመረው ሥራ ሊበረታታ የሚገባውና ለሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችም መልካም ተሞክሮ ያለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም የቆላማ አካባቢ በሽታዎች የደሃው ማኅበረሰብ ክፍል በሽታ እንደ መሆናቸው ሕክምና ለማግኘት አቅም የሌላቸው እናቶችንና ሕፃናትን ለበለጠ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ የሚዳርጉ መሆናቸውን ዶ/ር ደረጃ ጠቅሰዋል፡፡ የቆላማ አካባቢ በሽታዎችን ከሀገራችን ማጥፋት ጊዜ የማይሰጠው አንገብጋቢ ጉዳይ በመሆኑ ባለድርሻ አካላት በየክልሉ ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩ እንደሚገባና የተጀመሩ ሥራዎችም ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ሚኒስትር ዴኤታው አሳስበዋል፡፡

የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ሕይወት ሰለሞን እንደገለጹት ትኩረት የሚሹ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች በባክቴሪያ፣ በጥገኛ ህዋስና በቫይረስ አማካኝነት ሊከሰቱ የሚችሉ ሲሆኑ በዓለማችን ከ1.7 ቢሊየን በላይ የሚሆነው ኅብረተሰብ በበሽታዎቹ ሳቢያ ለሕመም፣ ለአካል ጉዳት፣ ለማኅበራዊና ለኢኮኖሚያዊ ችግር ይዳረጋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ዩኒቨርሲቲው እንደ ምርምር ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የምርምር መስኮች የልኅቀት ማዕከል ለመሆን እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው በምርምር ውጤቶች ላይ ተመሥርቶ በርካታ የማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራዎችንም እየሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው አሁናዊ ስትራቴጂክ ዕቅድ ላይ የምርምር ጥራትና አግባብነት የትኩረት ሥራ ሆኖ የተቀመጠ በመሆኑ በተዘነጉ ቆላማ አካባቢ በሽታዎች ዙሪያ ለሚሠሩ የምርምርና ሥልጠና ሥራዎች ዩኒቨርሲቲው አስፈላጊውን እገዛ ሁሉ እንደሚያደርግ ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡፡

የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ በበኩላቸው እንደ እግር እብጠት (ዝሆኔ)፣ ቁንጭርና ሌሎች የመሳሰሉት ትኩረት የሚሹ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች እንደ ዓለምም ሆነ እንደ ሀገር ከጊዜ ወደ ጊዜ በሰዎች ጤንነት፣ በማኅበራዊ ሕይወትና በኢኮኖሚው ላይ የሚያሳድሩት አሉታዊ ተፅዕኖ እጅግ በጣም ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡ ትኩረት የሚሹ የቆላማ አካባቢ በሽታዎችን መቆጣጠር የልማት ግቦችን ከማሳካት አንፃር ቁልፍ ተግባር መሆኑን ጠቅሰው እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ ሀገሮች በተለይ በአፍሪካ ደረጃ ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገሮች ትልቅ ቁጥር ያለው የኅብረተሰብ ክፍል በበሽታዎቹ እየተጎዳ እንዳለ ጠቁመዋል፡፡ ለዕውቀት ሽግግር፣ የትኩረት አቅጣጫዎችን የጋራ አድርጎ ለመውሰድ እንዲሁም እንደ ዩኒቨርሲቲ በራሳችን ተጨማሪ ተልዕኮ በመውሰድ ለአካባቢው፣ ለክልሉና ለሀገር የሚጠበቅብንን አስተዋፅኦ ለማበርከት የጉባዔው ፋይዳ የጎላ መሆኑን ተ/ፕ በኃይሉ ተናግረዋል፡፡

ትኩረት የሚሹ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች ምርምር ማዕከል የምርምር፣ የሥልጠናና የማማከር አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን በአርባ ምጭ ዙሪያ ባሉ ችግሮች ላይ የተሠሩ የተለያዩ የምርምር ውጤቶች በተለያዩ ጆርናሎች ላይ መታተማቸውን የማዕከሉ ዳይሬክተር አቶ ፀጋዬ ዮሐንስ ገልጸዋል፡፡

በአርባ ምንጭ ጤና ጣቢያና ሆስፒታል ትኩረት በሚሹ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች ላይ ሥልጠና እየሰጠን የመከላከልና በሽታውን የሚያመጡ ህዋሳትን ጭምር የመቆጣጠር ሥራ በመሥራት ለውጥ አምጥተናል ያሉት ዳይሬክተሩ በሀገር አቀፍ ደረጃ በትምህርት ቤት የሚሰጠውን የአንጀት ትላትል የመጻሕፍት ስርጭት ማካሄድ፣ በሀገራዊው የመድኃኒት ስርጭት ቁጥጥር ፕሮግራም አስፈላጊውን ድጋፍ መስጠትና በመድኃኒት ስርጭት ዙሪያ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚሠሩ ሥራዎችን ለማገዝ በተሠሩ ምርምሮች ፖሊሲዎችን እስከ ማስቀየር መቻሉ ማዕከሉ ካከናወናቸው ዐበይት ተግባራት መካከል መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

የክልሎች አፈፃፀም ግምገማ፣ የተሻሉ ልምዶችንና ግኝቶችን ማበረታታትና ለሌሎች ማስተማሪያ እንዲሆኑ መመዝገብ፣ ፕሮግራሙ ዘላቂነት እንዲኖረውና ኅብረተሰቡ የራሱን ጤና በእራሱ በሚጠብቅበት ሁኔታ ላይ መወያየት እና 3ኛው ማስተር ፕላን የደረሰበት ሁኔታ ግምገማ በጉባዔው በሰፊው የተዳሰሱ ጉዳዮች ናቸው፡፡

ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ጉባዔው ለቀጣይ ዓመት ዕቅድ እንደ ግብዓት የሚያገለግሉና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የሚያስችሉ ልምዶችና ተሞክሮዎች የተቀመሩበት ነው፡፡ በዘርፉ ለሚሠራው የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራ ስኬታማነት የጤና ተቋማት ብቻ ሳይሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካለት የበኩላቸውን ግዴታ በአግባቡ እንዲወጡም አሳስበዋል፡፡

የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ፣ የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ሕይወት ሰለሞን፣ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ፣ የክልል ጤና ቢሮ አስተባባሪዎችና ተሳታፊዎች፣ የአጋር ድርጅቶች ኃላፊዎችና አስተባባሪዎች፣ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት በፕሮግራሙ ተገኝተዋል፡፡

በፕሮግራሙ መጨረሻም በኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ የተመራው ልዑክ ቡድን የዩኒቨርሲቲውን ሪፈራልና ማስተማሪያ ሆስፒታል ግንባታ የጎበኘ ሲሆን ሆስፒታሉ በ2014 ዓ/ም ከፊል አገልግሎት መስጠት በሚጀምርበት ሁኔታና ከሚኒስቴር መ/ቤታቸው በሚደረጉ ቀጣይ ድጋፎች ዙሪያ ከዩኒቨርሲቲው የአስተዳደር ካውንስል አባላት ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡

 

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት