Print

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ማኅበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ ከኮሌጁ ዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ማስተባበሪያ ጽ/ቤት፣ ከጂኦግራፊና አካባቢ ጥናት ት/ክፍል እንዲሁም ከጀርመን ተራድኦ ድርጅት (GIZ) ጋር በመተባበር ከጋሞ ዞን ወረዳዎች ለተወጣጡ የተፈጥሮ ሀብትና ደን ልማት ባለሙያዎች በ‹‹Geographic Information System(GIS) እና ‹‹Global Positioning System››(GPS) ሶፍትዌሮች ዙሪያ ከሐምሌ 26 - ነሐሴ 1/2013 ዓ/ም ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የማኅበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ሙሉጌታ ደበሌ ሀገሪቱ ያላትን የተፈጥሮ ሀብት በዘላቂነት ለመጠቀምና ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ ከወዲሁ በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ለዚህም በቴክኖሎጂ የተደገፈ መረጃና አሠራር በአካባቢው የሚስተዋለውን የደን ሀብት ከጉዳት የሚታደግና የዘርፉን ባለሙያዎች ሥራ ውጤታማና የተቀላጠፈ ያደርገዋል ብለዋል፡፡

የኮሌጁ የዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኃ/ማርያም አጥናፉ እንደገለጹት ሥልጠናው ከሙያው ጋር ቀጥታ ግንኙነት ላላቸው ባለሙያዎች ተሰጥቷል፡፡ ይህም የደን ጥበቃና ቁጥጥር ሥርዓቱን ውጤታማና በቴክኖሎጂ የታገዘ ከማድረጉም ባሻገር ትክክለኛ መረጃ አደራጅቶ ከመያዝ እና ጊዜና ጉልበትን ከመቆጠብ እንፃርም ጉልህ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡

የጂኦግራፊና አካባቢ ጥናት ት/ክፍል መምህር ረ/ፕ ዓለሙ አሰሌ በበኩላቸው በሥልጠናው ያሉንን የዕጽዋት፣ የደን፣ የውሃና የመሳሰሉ የተፈጥሮ ሀብት መረጃ አቀናጅቶ በመያዝ የትና በምን ደረጃ ላይ እንዳሉ የሚከታተሉበት የተለያዩ የካርታ ሞዴሎችንና የመረጃ ምንጮችን አሳይተናል ብለዋል፡፡ የመረጃ አያያዝና ትንተና ንዑስ ሥርዓት፣ የካርታ አሠራር፣ ዓለም አቀፍ አቅጣጫ ጠቋሚ ዘዴዎችና ጂኦግራፊያዊ የመረጃ አያያዝ ዘዴዎች ላይ ግንዛቤ መፈጠሩንም ተናግረዋል፡፡

በGIZ የደን ሀብት አማካሪ የሆኑት አቶ ዓለሙ አሰፋ ድርጅታቸው ከመንግሥት ተቋማት ጋር ባለው ስምምነት መነሻነት በቴክኖሎጂዎች በመደገፍ የተቋማትን የመፈጸም አቅም ለማጎልበት እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡ ሥልጠናው ሀገሪቱ እያከናወነች ለምትገኘው የአረንጓዴ አሻራ እንቅስቃሴ ጉልህ ሚና የሚጫወት በመሆኑ ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው በመሥራት ልምዳቸውን ወደ ተግባር መቀየር አለባቸው ብለዋል፡፡

የሥልጠናው ተሳታፊዎች ሥልጠናው የጊዜ፣ የጉልበትና የገንዘብ ብክነትን የሚያስቀር ተአማኒ መረጃ ለማቅረብ የሚያስችል ዕውቀት ያገኙበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት