የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ አገልገሎት ዳይሬክቶሬት ከሁሉ አቀፍ ሴክተር ዳይሬክቶሬትና ከአርባ ምንጭ ከተማ ወጣቶች ሊግ ጽ/ቤት ጋር በመተባበር በአደንዛዥ ዕፅና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከከተማው 12 ቀጠናዎች 6 ቀበሌያት ለተወጣጡ ወጣቶች ከነሐሴ 19-20/2013 ዓ/ም ሥልጠና ሰጥቷል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ  

የዩኒቨርሲቲው ሁሉ አቀፍ ሴክተር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መርክነህ መኩሪያ እንደገለጹት ሥልጠናው በአርባ ምንጭ ከተማ የሚኖሩ ወጣቶችን ከሱስ የተላቀቁ፣ በመልካም ስብዕና የተገነቡ ዜጎች እንዲሆኑ ማድረግን አልሞ የተሰጠ ነው፡፡ ሥልጠናው የሥነ-አዕምሮ ውቅርን እና አደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚነት የሚያስከትለውን ጉዳት ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ሲሆን ከሥልጠናው ባሻገር ወጣቶቹ ያሉበትን የሱስ ደረጃ ከጅምር እስከ ከፍተኛ በመለየት ቀጣይነት ያለው ሥራ መሥራት አለብንም ብለዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ከተማ ብልፅግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ቀዳሚ በኩር በበኩላቸው ሥልጠናው የወጣቶችን እሳቤ የሚቀይርና በከተማው እየተስፋፋ ያለውን የአደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚነት የሚቀንስ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሠልጣኝ የእርሱነህ ሳሙኤል ሥልጠናው ወጣቶች ከሱስ ለመላቀቅ ጥረት እንዲያደርጉ የሚያግዝ መሆኑን ጠቅሶ በአደንዛዥ ዕፅ ዙሪያ ራሱን ለመጠበቅ እንዲሁም ሌሎችንም ለመምከር የሚያስችል ዕውቀት ማግኘቱን ገልጿል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት