አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በሰሜኑ የሀገራችን አካባቢዎች በተከሰተው ጦርነት ሳቢያ ለተፈናቀሉና ለተጎዱ ወገኖች የቁሳቁስና የምግብ ጥሬ ዕቃዎችን እንዲሁም ለአገር መከላከያ ሠራዊት የገንዘብና የደም ልገሳ ድጋፎችን እያካሄደ ይገኛል፡፡ 

ዩኒቨርሲቲው ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በወሎ ዩኒቨርሲቲ ለሚገኙ ወገኖች 1.5 ሚልየን ብር የሚያወጡ 700 የብርድ ልብሶችን፣ 240 ጥንድ አንሶላዎችንና 50 ኩንታል ፉርኖ ዱቄት ድጋፍ አድርጓል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ለመከላከያ ሠራዊት የአንድ ወር ደመወዙን የሰጠ ሲሆን 187 ዩኒት ደምም ተሰብስቧል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

ከዚህም ባሻገር በክረምት የበጎ አድራጎት ሥራ በአርባ ምንጭ ከተማ ለሚገኙ አቅመ ደካማ ወገኖችና ጧሪና ደጋፊ ለሌላቸው አረጋውያን የአዲስ ዓመት በዓልን ምክንያት በማድረግ የማዕድ ማጋራት መርሃ-ግብር ተካሂዷል፡፡ በፕሮግራሙም ለ200 ሰዎች ለእያንዳንዳቸው 10 ኪሎ ግራም ፉርኖ ዱቄት ድጋፍ ተደርጓል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከሜሪጆይ ኢትዮጵያ፣ ከጋሞ ዞን አስተዳደር እና ከአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ጋር የአረጋውያንና የሕፃናት ማዕከል ለማቋቋም የጋራ ስምምነትም ተፈራርሟል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደገለጹት በአሁኑ ወቅት ዩኒቨርሲቲው በአገራዊ ጉዳዮችም ሆነ የአካባቢውን ማኅበረሰብ በተመለከተ አበረታች ሥራዎችን እየሠራ ነው፡፡ ሰላም ለሁሉም ነገር መሠረት እንደመሆኑ በጦርነቱ ምክንያት ከቤታቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን በሞራልም ሆነ በገንዘብ መደገፍ እንዲሁም ወደ ቀደመ ሰላማቸው እንዲመለሱ የሚጠበቅብንን ሁሉ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡ ችግሩ እንደ ሀገር መፍትሄ እስከሚያገኝ ድረስ በአፋር አካባቢ ላሉ ወገኖችም ዩኒቨርሲቲውና የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ መሰል ድጋፉን እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

በወሎ ዩኒቨርሲቲ በመገኘት ድጋፉን ያበረከተውን ልዑክ የመሩት የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ገዝሙ ቀልቦ ስኬታማ የመማር ማስተማር እንዲኖር ሀገር ሰላም ልትሆን እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ከመላው የኢትዮጵያ አካባቢዎች የተገኙ እንደመሆናቸው ቤተሰቦቻቸው ላይ የሚደርሰው ችግር በትምህርታቸው ላይ ተፅዕኖ እንዳያሳድር የተቻለንን ድጋፍ ሁሉ ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት