ረ/ፕ ጊሹ ሰሙ ከአባታቸው አቶ ሰሙ ተሊላ እና ከእናታቸው ወ/ሮ የሺ ኡርጌ ሰኔ 12/1968 ዓ/ም በቀድሞው አርሲ ክፍለ ሀገር በአርባ ጉጉ አውራጃ ልዩ ስፍራው ጮሌ በምትባል ቦታ ተወለዱ፡፡

የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በጮሌ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት እንዲሁም የ2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በጭላሎ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ተከታትለዋል፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ1995 ዓ/ም በፊዚክስ ትምህርት ያገኙ ሲሆን 2ኛ ዲግሪያቸውን ከዚሁ ዩኒቨርሲቲ በ2004 ዓ/ም በማቴሪያል ሳይንስ አግኝተዋል፡፡

በጂማ ዞን ዴዶ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት በፊዚክስ መምህርነትና በምክትል ርዕሰ መምህርነት ያገለገሉት ረ/ፕ ጊሹ የካቲት 12/2000 ዓ/ም በፊዚክስ ት/ክፍል በረዳት ምሩቅ I አካዳሚክ ማዕረግ በመቀጠር አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲን ተቀላቅለዋል፡፡ የካቲት 12/2001 ዓ/ም ወደ ረዳት ምሩቅ II አካዳሚክ ማዕረግ የተሸጋገሩ ሲሆን ጥቅምት 29/2005 ዓ/ም ወደ ሌክቸረር አካዳሚክ ማዕረግ እንዲሁም የአገልግሎት ጊዜያቸውንና የምርምር ውጤታቸውን መሠረት በማድረግ የረዳት ፕሮፌሰር አካዳሚክ ማዕረግ አግኝተዋል፡፡

ረ/ፕ ጊሹ ከመምህርነታቸው ባሻገር የፊዚክስ ት/ክፍል ኃላፊና በተከታታይና ርቀት ትምህርት ኮሌጅ የተከታታይ ትምህርት ፕሮግራም አስተባባሪ በመሆን ሕይወታቸው እስካለፈበት ቀን ድረስ ዩኒቨርሲቲውን ላለፉት 13 ዓመታት አገልግለዋል፡፡ ባደረባቸው ሕመም በሕክምና ሲረዱ ቆይተው መስከረም 17/2014 ዓ/ም በተወለዱ በ46 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ ረ/ፕ ጊሹ ባለትዳርና የአንድ ወንድ ልጅ አባት ነበሩ፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በረ/ፕ ጊሹ ሰሙ ሞት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን እየገለጸ ለቤተሰቦቻቸው፣ ለሥራ ባልደረቦቻቸውና ለወዳጅ ዘመዶቻቸው መጽናናትን ይመኛል፡፡

 

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት