ረ/ፕ አባይነህ ኡናሾ ከአባታቸው ከአቶ ኡናሾ ጋንዲሌ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ፋስቴ ጡኖ በቀድሞው ጋሞ ጎፋ ጠቅላይ ግዛት ጋርዱላ አውራጃ ዘይሴ አካባቢ በ1950 ዓ/ም ተወለዱ፡፡

የ1ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በዘይሴና በጊዶሌ 1ኛ ደረጃ ት/ቤቶች እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በደብረ ዘይት ወንጌላዊት ኮሌጅ እና በአርባ ምንጭ 2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች ተከታትለዋል፡፡ በ1975 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በባዮሎጂ ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡

ከመስከረም 1/1976 - ሐምሌ 30/1980 ዓ.ም በዲላ ከፍተኛ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ከነሐሴ 01/1980 - ነሐሴ 30/1985 ዓ.ም በሶዶ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት፣ ከመስከረም 01/1986 - ሰኔ 30/1988 ዓ.ም በኮልፌ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በባዮሎጂ መምህርነት፣ ከሐምሌ 01/1988 - ነሐሴ 30/1993 ዓ.ም በመድኃኔ ዓለም አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት በም/ር/መምህርነት፣ ከመስከረም 01/1994 - ጥር 30/1996 ዓ.ም በድል በር 2ኛ ደረጃ ት/ቤት በም/ር/መምህርነት አገልግለዋል፡፡

ረ/ፕ አባይነህ ኡናሾ በ1997 ዓ.ም የ2ኛ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያገኙ ሲሆን ከጥቅምት 01/1998 ዓ.ም ጀምሮ በደቡብ ዩኒቨርሲቲ በዲላ መምህራን ትምህርትና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በባዮሎጂ ትምህርት ክፍል አገልግለዋል፡፡ ከግንቦት 01/2001 - መስከረም 05/2006 ዓ.ም በዲላ ዩኒቨርሲቲ የኤች አይ ቪ ጽ/ቤት ኃላፊ ሆነውም አገልግለዋል፡፡ ዲላ ዩኒቨርሲቲ እያገለገሉ ባሉበት ወቅት ከመማር ማስተማር ሥራቸው ጎን ለጎን በዘይሴ ብሔረሰብ ባህል ላይ ያተኮረ መጽሐፍ ‹‹የዘይሴ ብሔረሰብ ባህል›› በሚል ርዕስ በ1999 ዓ/ም ለኅትመት አብቅተዋል፡፡ በብዝሃ-ሕይወት፣ በኤች አይ ቪ/ኤድስና በሌሎችም ተዛማጅ ዘርፎች ላይ የምርምርና የተለያዩ ጽሑፎችን በማዘጋጀት በዓለም አቀፍ ጆርናሎችና ጋዜጦች ላይ አሳትመዋል፡፡ ግንቦት 13/2007 ዓ.ም በዲላ ዩኒቨርሲቲ በማስተማር ላይ ባሉበት ወቅት ወደ ረዳት ፕሮፌሰርነት አካዳሚክ ማዕረግ አድገዋል፡፡

ረ/ፕ አባይነህ ኡናሾ ከጥር 2009 ዓ/ም ጀምሮ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲን የተቀላቀሉ ሲሆን በነበራቸው ቆይታ በርካታ የድኅረ ምረቃ ተማሪዎችን በማስተማርና በማማከር ለምርቃት አብቅተዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓትም የድኅረ ምረቃ ተማሪዎችን እያማከሩ ባሉበት ባጋጠማቸው ድንገተኛ ሕመም መስከረም 18/2014 ዓ/ም በ64 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡

ረ/ፕ አባይነህ ኡናሾ ባለትዳርና የሁለት ወንድና የሁለት ሴት ልጆች አባት ነበሩ፡፡ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በረ/ፕ አባይነህ ኡናሾ ድንገተኛ ኅልፈተ ሕይወት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን እየገለጸ ለቤተሰቦቻቸው፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸውና ለሥራ ባልደረቦቻቸው መጽናናትን ይመኛል፡፡

 

       የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት