ለ1 ወር በተለያዩ ጤና ጣቢያዎች በቡድን ሥልጠና ፕሮግራም/Team Training Program/TTP/ ላይ የቆዩ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ተመራቂ ተማሪዎች የመጨረሻ ሪፖርታቸውን ገምገሚ መምህራን በተገኙበት ከመስከረም 14-15/2014 ዓ/ም መስክ በወጡባቸው ጤና ጣቢያዎች አቅርበዋል፡፡ ቆላ ሼሌ፣ ኮንሶ ካራት፣ አረካ፣ ቦዲቲና ብርብር ጤና አጠባበቅ ጣቢያዎች ተማሪዎቹ በሥራ የቆዩባቸው የጤና ተቋማት ናቸው፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ    

የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ደስታ ሀብቱ እንደገለጹት የቡድን ሥልጠና ፕሮግራም ከተለያዩ ት/ክፍሎች የተወጣጡ ተመራቂ ተማሪዎች በቡድን ወደ ጤና ተቋማት ወርደው ከኅበረተሰብ ጤና ጋር የተያያዙ ችግሮችን በመለየት ለመፍታት የሚሠሩበት እንዲሁም በጤና ተቋማቱ ሥር በመሆን በየዘርፋቸው የሕክምና አገልግሎት የሚሰጡበት ፕሮግራም ነው፡፡ ፕሮግራሙ በዋናነት ተማሪዎች በቡድን የመሥራት መንፈስን እንዲያጎለብቱ፣ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በጋራ የመሥራት ልምድን እንዲያካብቱ፣ እርስ በእርስና ከሌሎች ጋር ሊኖር የሚገባን የተግባቦት ክሂሎት እንዲያዳብሩ እንዲሁም ተማሪዎች ገሃዱን የሥራ ዓለም ከነተግዳሮቱ እንዲለማመዱ ለማድረግ እንደሚዘጋጅ ተናግረዋል፡፡

ፕሮግራሙ ብቁና ጥራት ያላቸው የጤና ባለሙያዎችን ከማፍራት አንፃር ሚናው የጎላ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ደስታ በዚህኛው ዙርም ተማሪዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ የጤና ተቋማትን፣ ሌሎች ከጤና ጋር ግንኙነት ያላቸውን የሥራ ዘርፎች እንዲሁም ማኅበረሰቡን የሚጠቅሙ በርካታ ተግባራትን ማከናወናቸውን ካቀረቡት ሪፖርትና ካደረግነው ምልከታ አረጋግጠናል ብለዋል፡፡

ከተማሪዎቹ መካከል በቆላ ሼሌ ጤና አጠባበቅ ጣቢያ የቆየችው የነርሲንግ ት/ክፍል ተመራቂ ተማሪ ኢየሩሳሌም መንበሩ እንደገለጸችው በቆይታቸው በጤና ጣቢያው በድንገተኛ፣ በእናቶች ማዋለጃ፣ በተመላላሽ ታካሚዎች፣ በላቦራቶሪዎችና በሌሎች ክፍሎች በመገኘት የሕክምና አገልግሎት ሰጥተዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ቤት ለቤት በመንቀሳቀስ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ችግሮችን ለይተው ለማኅበረሰቡ የጤና ትምህርት መስጠታቸውን በቆይታዋም ለቀጣይ ሥራዋ አጋዥ የሆኑ ሙያዊ ዕውቀትና ክሂሎት ማግኘቷን ተናግራለች፡፡

በኮንሶ ካራት ጤና አጠባብቅ ጣቢያ በመሰል ሥራ ላይ የቆየው የማኅበረሰብ ጤና ት/ክፍል ተመራቂ ተማሪ የዓለምዘርፍ አገኘሁ በበኩሉ ከዚህ ቀደም ለተግባር ልምምድ ሲወጡ የአንድ ትምህርት መስክ ተማሪዎች በአንድ ላይ እንደሚወጡ አስታውሶ በአሁኑ ፕሮግራም ከተለያዩ የትምህርት መስኮች የተወጣጡ በመሆናቸው አዳዲስ ዕውቀትና ክሂሎት መለዋወጣቸውንና በጋራ የመሥራት ልምድ ማካበታቸውን ተናግሯል፡፡

በቦዲቲ ጤና አጠባበቅ ጣቢያ በዚሁ ሥራ ላይ የቆየችው የሚድዋይፍሪ ተመራቂ ተማሪ ምኅረት ታፈሰ በጤና ጣቢያውና በአካባቢው በነበረን ቆይታ የሕክምና አገልግሎት ከመስጠታችን ባሻገር በጤና ጣቢያው ካርድ ክፍል፣ ከእናቶች ማዋለጃና ከደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ የአደረጃጀት ችግሮችን ለመቅረፍ ከጤና ጣቢያው፣ ከከተማ አስተዳደሩና

ከማኅበረሰቡ ገንዘብ በማሰባሰብ የጤና ጣቢያውን አሠራርና አገልግሎት አሰጣጥ የተሻለ እንዲሆን አድርገናል ብላለች፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የወጣቶች የሥነ-ተዋልዶ ምክርና አገልግሎት መስጫ ክፍልን በማደራጀት አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረጋቸውን የምትናገረው ተማሪዋ በአጠቃለይ ፕሮግራሙ የወደፊት የሥራ አካባቢያችንና የምናገለግለው ማኅበረሰብ ምን እንደሚመስል ያየንበትና ትምህርት የወሰድንበት ነበር ብላለች፡፡

በወላይታ ዞን የቦዲቲ ጤና አጠባበቅ ጣቢያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ተካልኝ አሻሌ ተማሪዎቹ በጤና ጣቢያው በነበራቸው ቆይታ የዕረፍት ቀናትንና ምሽቱን ጨምሮ እንደ ተማሪ ሳይሆን ልምድ እንዳለው ባለሙያ በተለያዩ ዋርዶች ከጤና ጣቢያው ባለሙያዎች ጋር በመሆን ሲሠሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡ ተማሪዎቹ በጤና ጣቢያችን በካርድ ክፍልና በእናቶች ማዋለጃ ክፍሎች የሚታዩ የአደረጃጀት ችግሮችን በመለየት ማስተካከያ ያደረጉ ሲሆን የጤና ጣቢያውን የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃም አዘጋጅተዋል ብለዋል፡፡ ተማሪዎቹ በነበራቸው ቆይታ በጤና ጣቢያው እንዲሁም እስከ ጤና ኬላዎች ድረስ በመውረድ ለማኅበረሰቡ ለሰጡት ግልጋሎት ያላቸውን ምስጋናም ሥራ አስኪያጁ አቅርበዋል፡፡

መሰል ፕሮግራሞች ተማሪዎች ወደ ሥራው ዓለም ከመቀላቀላቸው በፊት በትብብር የመሥራት መንፈስን፣ የእርስ በእርስ የዕውቀትና ልምድ ልውውጥን እንዲሁም ወደ ፊት የሚሠሩባቸው ተቋማትና የሥራ አካባቢን እንዲለማመዱ ከማድረግ አንፃር ፋይዳው የጎላ በመሆኑ መሰል ፕሮግራሞች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት